በአዲስ አበባ ከተማ ከ1 ሺህ 600 በላይ የግል የትምህርት ተቋማት እንዳሉ የተገለጸ ሲሆን፣ 276 አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ዘርፉን በ2018 የትምህርት ዘመን ይቀላቀላሉ ተብሏል።
የአዲስ አበባ ከተማ የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን እና የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ በጋራ ያዘጋጁት የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በውይይት መድረኩ በትምህርት ቤቶች በአገልግሎት ክፍያ ጭማሪ ያለውን አለመግባባት ለመፍታት የሚያስችሉ ሀሳቦች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ምክንያታዊ የሆኑ ጭማሪዎች አስፈላጊ መሆናቸውን የገለጸው የአዲስ አበባ ከተማ የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን፣ በሌላ በኩል ከ100 እስከ 260 በመቶ ጭማሪ የጠየቁ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን ጠቁሟል፡፡
ይህን መሰል ጭማሪ መደረጋቸው ተገቢነት የሌላቸው መሆኑ ታምኖበት ውሳኔ መሰጠቱን አስታውቋል።
በውይይት መድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ(ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ከተማ የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኢዘዲን ሙስባህ፣ የትምህርት ቤት ባለቤቶች እና የወላጅ ተወካዮች ተገኝተዋል።
በበላይሁን ፍሰሀ