የግል ባለሃብቶችን በማስተባበር የተጀመሩ ሰው ተኮር የበጎ ፈቃድ የልማት ስራዎች በክረምቱ መርሐ-ግብርም ተጠናክረው መቀጠላቸው ተገለጸ

You are currently viewing የግል ባለሃብቶችን በማስተባበር የተጀመሩ ሰው ተኮር የበጎ ፈቃድ የልማት ስራዎች በክረምቱ መርሐ-ግብርም ተጠናክረው መቀጠላቸው ተገለጸ

AMN – ሐምሌ 2/2017 ዓ.ም

የግል ባለሃብቶችን በማስተባበር የተጀመሩ ሰው ተኮር የበጎ ፈቃድ የልማት ስራዎች በክረምቱ መርሐ-ግብርም ተጠናክረው መቀጠላቸው ተገልጿል፡፡

የበጎ ፈቃድ ስራዉ በመዲናችን የሚገኙ የበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን ችግሮች በመፍታት ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ዛሬም በመዲናዋ የክረምት በጎ ፈቃድ ስራዎች ተጠናክረው የቀጠሉ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኦሮሚያ ባንክ ጋር በመተባበር በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ለአቅመ ደካሞች መኖሪያነት የሚያገለግል ባለ 4 ወለል ህንፃ ግንባታ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ተካሂዷል፡፡

በመርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ እና የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ አለምፀሃይ ሽፈራው፣ ከተማ አስተዳደሩ ላለፉት ዓመታት በርካታ ሰው ተኮር የልማት ስራዎችን እያከናወነ እና የህዝብን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ስንተባበር እና በጋራ ስንቆም የማንወጣቸው ችግሮች አይኖሩም፤ በዚህም እንደሀገር በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊ፣ በፖለቲካ እና በዲፕሎማሲ ዘርፍ አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ እንችላለ ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ እሸቱ ለማ (ዶ/ር )፣ የበጎ ፈቃደኝነት ስራ ባለፉት ዓመታት በጥልቀት በመሰራቱ ባህል እየሆነ መጥቷል፤ በዚህም የበርካቶችን ህይወት ማሻሻል ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኦሮሚያ ባንክ ቦርድ ሰብሳቢ አሰፋ ስሜ (ዶ/ር)፣ ባንኩ ቀደምሲል ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በዚህ መሰል የበጎ ፈቃድ ተግባር በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው፣ ወደፊትም በዚህ ረገድ የምናደርገውን ተሳትፎ አጠናክረን ማህበራዊ ኃላፊነታችንን እንወጣለንም ብለዋል፡፡

በታምሩ ደምሴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review