የአዲስ አበባ ከተማን የመንገድ መሰረተ ልማት በሚፈለገው ደረጃ ለማሳደግ እና ተደራሽነቱን ለማስፋት የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ሰራተኞች እና በየደረጃው የሚገኘው አመራር የበለጠ መትጋት እና ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በ2017 በጀት አመት 31 ነጥብ 5 ኪሎሜትር ርዝመት ያላቸው 13 የመንገድ ፕሮጀክቶች እና 8 ድልድዮች ተጠናቀው ለምረቃ እንዲበቁ በማድረግ እና በአጠቃላይ በበጀት አመቱ በመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታው መስክ ለተገኘው ስኬት ለሰራተኞቹ የምስጋና እና የእውቅና መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት በተካሄደው የምስጋና እና እውቅና መርሃ ግብር ላይ በተለይም ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ምንም ማሻሻያ ሳይደረግበት የቆየው የባስልጣን መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች የደረጃ እድገት እና የደሞዝ ማሻሻያ ጥናት በከተማ አስተዳደሩ ተፈቅዶ እና ጸድቆ ይፋ ተደርጓል፡፡
የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች በተለይም በዝቅተኛ እርከን ላይ የሚገኙት በአነስተኛ ደሞዝ ሳይከፉ 24/7 በመስራት ከተማዋን ብሎም ሀገርን የሚያኮራ የልማት ስራን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል፡፡
የከተማ አስተደዳሩ ሰራተኞችን የበለጠ ለማበረታታት እና አሁን ከተማዋ እያካሄደች ካለችው ዘርፈ ብዙ የልማት ስራ አንጻር የበለጠ ተግተው እንዲሰሩ ለማነሳሳት የደረጃ እድገት እና የደሞዝ ማሻሻያው ተጠንቶ እንዲጸድቅ መፍቀዱንም ገልጸዋል፡፡
መስራት ያስከብራል ፤ከልብ መስራት እና ውጤት ማስመዝገብም ያኮራል፤ትጋትም ያሸልማል ያሉት ከንቲባ አዳነች የአዲስ አበባ የመንገድ ሽፋን ገና ብዙ መስራት ይጠይቃል ብለዋል፡፡
ከተማችን አለም አቀፍ ተወዳዳሪ እስክትሆን ድረስ እልህ በመሰነቅ ፣ የተሰጣችሁ እውቅና የበለጠ ሞራል ሆኗችሁ ከቀድሞው በላይ ጥራትን በመጨመር ፣ ብክነትን በማስወገድ፣ ፍጥነትን በማሳደግ እና ሌብነትን በመዋጋት 24/7 ልትሰሩ ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ በመንገድ መሰረተ ልማት መስክ በራስ አቅም እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን የገለጹት ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣንን አቅም በሎጀስቲክስ እና በሰው ሀይል የማጠናከር እና ሰራተኞቹንም በልዩ ልዩ ሁኔታ የማትጋት እና የማበረታታት ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡
በሰብስቤ ባዩ