የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የስማርት ፖሊስ ስቴሽን ማልማት የሚያስችል የውል ስምምነት ተፈራረሙ

You are currently viewing የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የስማርት ፖሊስ ስቴሽን ማልማት የሚያስችል የውል ስምምነት ተፈራረሙ

AMN ሀምሌ 02 ቀን 2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የስማርት ፖሊስ ስቴሽን ማልማት የሚያስችል የውል ስምምነት በዋናው መስሪያ ቤት ተፈራርመዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በስምምነቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር ከአሁን በፊት EFPAPP ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በማበልፀግ የኢትዮጵያ ፖሊስ በአህጉርና በዓለም ዓቀፍ መድረኮች ተወዳዳሪ እና አሸናፊ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደነበረው አስታውሰው የተገኘው ድል እንደ ሀገር እና እንደ ፖሊስ የሚያኮራ መሆኑን ገልፀዋል።

ኮሚሽነር ጀነራል የምንገነባው የስማርት ፖሊስ ስቴሽን የኢትዮጵያ ፖሊስን በአፍሪካ የመጀመሪያ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ በአራተኛ ደረጃ ላይ የሚያስቀምጠው መሆኑን አንስተው ይህም ህዝባችን የፖሊስን አገልግሎት እና መረጃዎችን በነፃነት እንዲያገኝ፤ የፖሊስን ስራ በላቀ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማገዝ እያደረግነው ያለውን ከፍተኛ ጥረት የሚያመላክትና ለአፍሪካ ሀገራትም ትልቅ የመነሳሻ ሞዴል ሆኖ የሚታይ መሆኑን ገልፀዋል።

መንግስት በለውጡ ለፀጥታ ተቋማት በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት የኢትዮጵያ ፖሊስ የአፍሪካ ፖሊስ የቴክኖሎጂ መነሻ፤ የዘመናዊ ፖሊስ ግንባታ ምሳሌ መሆኑን ያነሱት ክቡር ኮሚሽነር ጀነራል ለተገኘው ብሔራዊ ኩራትና ድል ሌትተቀን ከጎናችን በመሆን ስትተጉ ለነበራችሁ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የማኔጅመንትና በየደረጃው ላሉ አመራርና አባላት በራሳቸውና በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በበኩላቸው ሁለቱ ተቋማት እንደ ሀገር በጋራ ዕውቀትና ትብብር ባከናወኗቸው ስራዎች በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅናና ሽልማቶች መገኘታቸው እንደ ተቋም ትልቅ መነሳሻ እንደሚሆን ገልፀዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ በስምምቱ መሠረት ለአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት የሚሆን ጥራት ያለው የስማርት ፖሊስ ስቴሽን በታቀደለት ጊዜ ገንብተው ለማስረከብ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንሲቲትዩት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ይሰራሉ ማለታዉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ዳይሮክተሬት ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ በላከዉ መረጃ አስታወቁቋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review