በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት ሀገራዊ ጥቅምን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ስኬታማ የውጭ ግንኙነት ስራዎች መሰራታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በሰጡት የበጀት ዓመቱ የማጠቃለያ መግለጫ፣ በዲፕሎማሲ ዘርፍ ሀገር የተሻለ ጥቅም ማግኘት የሚያስችሏት ጥረቶችን ስለማድረጓ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ከሀገራት ጋር ያላትን ወዳጅነት ለማጠናከር፣ ቀጠናዊ ትስስር ለመመስረት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጎልበት በትጋት መስራቷንም ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል።
ጎረቤት ሀገራትን በመሰረተ ልማት የማስተሳሰር፣ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የማድረግ እና በሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ግንኙነት እንዲጎለብት ኢትዮጵያ በትኩረት የሰራችበት ዓመት ነበርም ብለዋል።
በዚህ ረገድ 11 የሚደርሱ የትብብር እና አጋርነት ስምምነቶች በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቁ መደረጉንም አውስተዋል።
ለአልሚዎች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር በማስገንዘብ ረገድም 806 ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት ስለማድረጋቸው ተናግረዋል።
በተለያዩ ውጭ ሀገራት በአስቸጋሪ ህይወት ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ደህንነት ለማስጠበቅ በተከወነ የተደራጀ ብሔራዊ ጥረትም ከ1 መቶ 1 ሺህ በላይ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መመለስ መቻሉን ገልፀዋል።
በአቡ ቻሌ