የባለብዙ ወገን ትብብር ለአፍሪካ ወረቀት ላይ ከሰፈረ ፅንሰ ሀሳብ ባለፈ የማንነቷ መገለጫ እና የግንኙነቷ መሰረታዊ አጀንዳ ነው ሲሉ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ገለጹ።
47ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በኢኳቶሪያል ጊኒ ማላቦ ተጀምሯል።
በስብሰባው ላይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ እና የኮሚሽኑ ባለስልጣናት፣ የህብረቱ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የህብረቱ ቢሮዎች እና አደረጃጀቶች ተወካዮች፣ የቀጣናዊ ኢኮኖሚ ማህበረሰቦች ኃላፊዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች እና ሌሎች ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል።
ዋና ፀሐፊው የባለብዙ ወገን ትብብር ለአፍሪካ ወረቀት ላይ የሰፈረ ጽንሰ ሀሳብ ብቻ ሳይሆን የማንነት መገለጫዋ እንደሆነ ገልጸዋል።
አፍሪካ በታሪኳ የገጠሟትን ፈተናዎች በአንድነት እና የጋራ ምላሽ መሻገሯን ጠቅሰው የጋራ እሴቶቹ የአፍሪካን መጻኢ ጊዜ ለመቅረጽ ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የኢጋድ ዋና ፀሐፊ የቀጣናዊ ኢኮኖሚ ማህበረሰቦች የጋራ ትብብር ማዕቀፍ ሊቀ መንበርም ናቸው።
ከስብሰባው ጎን ለጎን በሊቀ መንበርነት የሚመሩት የጋራ ትብብር ማዕቀፍ ስራዎች ያሉበትን ደረጃ አስመልክተው ሪፖርት እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።
ማዕቀፉ ቀጣናዊ ትስስርን ማጠናከር እና በአፍሪካ ህብረትና በቀጣናዊ ማህበረሰቦች መካከል ያለውን ትብብር የበለጠ የማጎልበት አላማ እንዳለው አመልክተዋል።
ኢጋድ ከአፍሪካ ህብረት እና ከእህት ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች ጋር በጋራ በመሆን ሰላማዊ፣ የተሳሰረች እና የበለጸገች አፍሪካ ግንባታ ለማሳካት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ መናገራቸውን ኢዜአ ከኢጋድ ሴክሬተሪያት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ከምክር ቤቱ ስብሰባ ጎን ለጎን ሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም የህብረቱ የ7ተኛ የመንፈቅ ዓመት የባለድርሻ አካላት የትብብር ስብሰባ ይደረጋል።
በስብስባው የአጀንዳ 2063 አፈጻጸም ግምገማ የሚገመገም ሲሆን የአፍሪካ ህብረት እና ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች ትብብር ያለበትን ደረጃ ውይይት ይደረግበታል።
የእ.አ.አ የ2026 የአፍሪካ ህብረት በጀት፣ የባለብዝሃ ወገን የአጋርነት ስትራቴጂ እና የህብረቱ የ2025 መሪ ሀሳብ አፈጻጸም ግምገማ ይካሄዳል።