በበጀት አመቱ የመዲናዋን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ የሠላም ሠራዊት አደረጃጀቶችን እና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ሕዝቡን የሰላም ባለቤት ማድረግ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
3ኛዉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤዉን በአድዋ ድል መታሰቢያ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በ2017 በጀት ዓመት የተከናወኑ ዋና ዋናተግባራት ፤ የተገኙ ውጤቶች ፣ በሂደቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና የቀጣይ በጀት ዓመት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡
በሰላምና ጸጥታ ዘርፍ በመዲናዋ የተከናወኑ ስራዎችን አስመልክቶ ኅብረተሰቡ በሰላም ግንባታ ላይ ያለውን ተሳትፎ ለማጎልበት በአካባቢ ሠላም፣ በአብሮነትና ትብብር ፤ በሰላም እሴት ግንባታ የግንዛቤ ማስጨበጫና የምክክር መድረኮች ማካሄዳቸዉን አንስተዋል፡፡
የሠላም ሠራዊት አደረጃጀቶችን እና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ አካባቢን በመጠበቅ ፣ ለወንጀለኞች መደበቂያ ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎችን በማጽዳትና የሥጋት ቦታዎችን ለይቶ በመከላከል ሕዝቡን የሰላም ባለቤት ማድረግ መቻሉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡
ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ሃሰተኛ ሰነድ፣ ከባድና ቀላል ወንጀል፣ የትምህርት ተቋማት ደህንነት፣ ለፀጥታና ደህንነት አስጊ የሆኑ ሁኔታዎችንና ግጭቶችን ከመከላከል ረገድ አበረታች ዉጤት መመዝገቡን አንስተዋል፡፡
የተለያዩ አዋኪ ድርጊቶችን ጨምሮ ከኢኮኖሚ አሻጥርና ህገ ወጥ የንግድ ቁጥጥር ጋር በተያያዘ ከሌሎች ሕግ አስከባሪ አካላት ጋር በመቀናጀት 11ሺህ 517 የወንጀል ድርጊቶችና የጸጥታ ስጋቶችን የመለየት፣ የመከላከል እና እርምጃ እንዲወሰድ የማድረግ ሥራ መሰራቱን ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሪፖርታቸዉ አንስተዋል፡፡
ከከተማዉ ፖሊስ እና ከተለያዩ የጸጥታ ተቋማት ጋር በተሰራዉ ወንጀል የመከላከልና ሰላም የማስጠበቅ አበረታች ዉጤቶች መገኘታቸዉን እና
መዲናዋ ሃገር አቀፍና አለም አቀፍ ሁነቶችን በተሳካ መንገድ ማስተናገድ መቻሏንም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡