በበጀት ዓመቱ 347 አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ ማድረግ መቻሉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ

You are currently viewing በበጀት ዓመቱ 347 አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ ማድረግ መቻሉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ

AMN – ሐምሌ 04/2017 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛና የበጀት አመቱን ማጠቃለያ ጉባኤ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

በጉባኤው ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸምን ሪፖርት ለምክር ቤቱ እያቀረቡ ይገኛሉ።

በበጀት አመቱ በተቋም ግንባታ ላይ በትኩረት መሰራቱን የገለፁት ከንቲባዋ፣ በአደረጃጀት፣ በአሠራር፣ በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል እና ምቹ የሥራ አካባቢን በመፍጠር ረገድ ተቋማዊ ሪፎርም ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

በዚህም በተቋማት የሕፃናት ማቆያዎችን በመገንባት ከ2 ሺህ117 በላይ የመንግስት ሰራተኛ ልጆችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

ከንቲባዋ አክለውም፣ በየደረጃው ከ185 በላይ የሰራተኞች ካፍቴሪያ እና ከ150 በላይ የሸማች ሱቆችን ወደ ስራ በማስገባት ሰራተኛው የኑሮ ውድነቱን መቋቋም የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።

በሌላ በኩል 21 ሺህ 46 የተገልጋይ ማረፊያዎችን በማዘጋጀት ምቹ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት መገንባታቸውንም ከንቲባ አዳነች አመላክተዋል።

በቴክኖሎጂ ረገድም 347 አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ ማድረግ መቻሉን የተናገሩት ከንቲባዋ፣ በዚህም በተቋማት ውስጥ በርካታ ለውጦችን ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል።

አገልግሎቶች ዲጂታላይዝ መደረጋቸው አገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋ፣ ጥራት ያለው እና ውጤታማ እንዲሆን ማስቻሉንም አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም የአገልግሎት አሰጣጡ በዲጂታል መታገዙ ብልሹ አሰራርን እና ብክነትን ለመቀነስ፣ የተገልጋይ እንግልትንና ምልልስን በማስቀረት እና የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ለመቀነስ አስችሏል ብለዋል ብለዋል ከንቲባ አዳነች፡፡

በአገልግሎት አሰጣጥ በርካታ ለውጦች ቢመዘገቡም፣ አሁንም ህዝቡን የሚያማርሩ ጉቦ የሚጠይቁ፣ ከደላላ ጋር በመተሳሰር ተገልጋይን የሚያንገላቱ የተለያዩ ተቋማት ውስጥ የሚታዩ ችግሮች መኖራቸውን እና በዚህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት በመስጠት የሚሰራ መሆኑንም ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል፡፡

በሊያት ካሳሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review