ተቋማትን በቴክኖሎጂ በማደራጃት የመንግስትንና የሕዝብን ሃብት ከብክነትና ከብልሹ አሰራር መታደግ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ እና የበጀት ዓመቱን ማጠቃለያ ጉባኤ በአድዋ ድል መታሰቢያ እያካሄደ ይገኛል፡፡
በጉባኤው ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸምን ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
የመዲናዋን የንብረት አስተዳደር በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን ለማድረግ የለማውን የንብረት አስተዳደር አሴት ማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲሰተም በመጠቀም በ 604 ተቋማት ላይ መተግበሩን ገልጸዋል፡፡
በዚህም በዓይነት 492 ሺህ 102 ንብረቶችን እና 6 ሺህ 810 ሕንጻዎችን በመረጃ ቋት በማስገባት የመንግስትና ሕዝብ ሀብትን ከብክነትና ከብልሹ አሠራር ማዳን መቻሉን ከንቲባ አዳነች ተናግረዋል።
ከንቲባዋ አክለውም፣ ከጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም ጀምሮ በተደረገ ንቅናቄ 2.8 ሚሊየን የሚሆኑ የመዲናዋ ነዋሪዎች ለፋይዳ መታወቂያ የተመዘገቡ ሲሆን በስራ ላይ ያለውን የኤጀንሲዉን ሲስተም ለመተካት እየተሰራ ያለው ስራም በጥቂት ወራት ውስጥ ተጠናቆ ወደ ስራ ይገባል ብለዋል፡፡
የሕንፃ ሕግጋትንና የከተማ መዋቅራዊ ፕላንን መሠረት ያደረገ የግንባታ ፈቃድ አሰጣጥን ከማሳደግ አኳያ ለ26 ሺህ 659 ተገልጋዮች የግንባታ ፈቃድ መሰጠቱንም ከንቲባዋ አንስተዋል፡፡
በቶለሳ መብራቴ