በአዲስ አበባ ከተማ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ፕሮግራም ተጠቃሚዎች ቁጥር 2.5 ሚሊየን መድረሱን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ

You are currently viewing በአዲስ አበባ ከተማ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ፕሮግራም ተጠቃሚዎች ቁጥር 2.5 ሚሊየን መድረሱን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ

AMN- ሐምሌ 4/2017 ዓ.ም

3ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን በዓድዋ ድል መታሰቢያ እያካሄደ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአስተዳደሩን የ2017 በጀት ዓመት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

ከንቲባዋ በሪፖርታቸው፣ የጤና አገልግሎቱን ተደራሽነት በተቀመጡ መስፈርቶች መሰረት በማሳካት እና የአገልግሎት ፍትሃዊነትና ጥራትንም በየጊዜው በማሻሻል በዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ስታንዳርድ መለኪያዎች መሠራቱን አብራርተዋል።

በበጀት አመቱ በሰለጠነ ባለሙያ የሚሰጥ የወሊድ አገልግሎት ከ170 ሺህ በላይ ለሚሆኑ እናቶች መሰጠቱን የገለጹት ከንቲባዋ፣ የተመላላሽ ህክምና ተጠቃሚነት ቁጥርን በድግግሞሽ 16.6 ሚሊየን ጊዜ መስጠት መቻሉን አንስተዋል፡፡

በተያያዘ በአስተኝቶ ህክምና ከ246 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተገልጋዮች ተደራሽ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡

በበጀት አመቱ የጤና እገልግሎት ፍትሃዊነትን ከማሳደግ አኳያ በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ፕሮግራም ተጠቃሚዎችን ቁጥር 2.5 ሚሊየን ማድረስ ተችሏል ብለዋል፡፡

ለዚህም የከተማ አስተዳደሩ ፕሮግራሙን ለመደገፍ በበጀት አመቱ ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ ድጎማ ማድረጉን ከንቲባ አዳነች አብራርተዋል።

በከተማዋ ሁለት አዲስ ግዙፍ አጠቃላይ ሪፈራል ሆስፒታሎች ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባዋ፣ በጥሩነሽ ቤጅንግ፣ በራስ ደስታ፣ በዘውዲቱ እና በሚኒልክ ሆስፒታሎች እየተሰራ ያለው ግዙፍ የማስፋፊያ ስራ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የስምንት አዳዲስ ጤና ጣቢያዎች ግንባታቸው የተጠናቀቀ መሆኑንና በቅርቡ ስራ የሚጀምሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአጠቃላይ በበጀት አመቱ በጤናው ዘርፍ 28 የግንባታ ፕሮጀክቶች እውን መደረጋቸውን ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡

የጤና መረጃ ስርዓቱን ሙሉ በሙሉ ወረቀት አልባ ያደረጉ የጤና ተቋማት ቁጥር 57 መድረሳቸውንም አብራርተዋል፡፡

በሚካኤል ህሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review