የኑሮ ውድነትን ለማቃለል የተሰራው ስራ ውጤት ማምጣቱን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ

You are currently viewing የኑሮ ውድነትን ለማቃለል የተሰራው ስራ ውጤት ማምጣቱን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ

AMN- ሐምሌ 4/2017 ዓ.ም

የኑሮ ውድነትን ለማቃለል እና የምርት አቅርቦት ክፍተቱን ለማጥበብ የተሰራው ስራ ውጤት ማምጣቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ እና የበጀት አመቱን ማጠቃለያ ጉባኤ እያካሄደ ይገኛል፡፡

በጉባኤው ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በበጀት አመቱ በንግዱ ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትን አቅርበዋል፡፡

ሚዛናዊ እና ፍትሃዊ የንግድ ሥርዓት በማስፈን ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓት እንዲዘረጋ መሰራቱን ያነሱት ከንቲባዋ፣ በህገ ወጥ ንግድ ሥራ ላይ በተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ መቀጠሉን ጠቁመዋል።

የኑሮ ውድነትን ለማቅለል እና የምርት አቅርቦት ክፍተቱን ለማጥበብ ታቅዶ መሰራቱ ትልቅ ለውጥ እንዳመጣ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አንስተዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በተለይ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች ወደ ከተማዋ እንዲገቡ የሰራው ስራ አመርቂ ነበር ብለዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ 3.5 ሚሊየን ኩንታል ምርት ወደ ከተማዋ መግባቱን ያነሱት ከንቲባ አዳነች፣ ይህም እቅዱን መቶ በመቶ ያሳካ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

አምራችና ሸማቹ በቀጥታ ግብይት የሚፈፅምባቸው የቅዳሜና እሁድ የገበያ ቦታዎችን ከ193 ወደ 219 በማሳደግ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለከተማ ነዋሪው እንዲቀርብ መደረጉ ገበያውን በማረጋጋት ረገድ ትልቅ ሚና ነበረው ብለዋል፡፡

በድጎማ ለሚቀርቡ ምርቶች በበጀት አመቱ ከተያዘው ከ14 ቢሊየን ብር በላይ በመደጎም የኑሮ ጫናን ለማቃለል እንደተሰራ ከንቲባዋ በሪፖርታቸው አመላክተዋል፡፡

የዳቦ አቅርቦትን ለመጨመር በመንግስትና በግል ባለ ሃብቶች አጋርነት የተገነቡ 26 ፋብሪካዎችን ወደ ስራ በማስገባት የነዋሪውን የኑሮ ጫና ለመቀነስ ጥረት መደረጉም በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

በተመሳሳይ በቀን አንድ ጊዜ ምግብ የማግኘት ችግር ለነበረባቸው ነዋሪዎች በ26 የምገባ ማእከላት በቀን እስከ 36 ሺህ ሰዎችን መመገብ መቻሉንም ከንቲባዋ በሪፖርታቸው አንስተዋል፡፡

የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ የምርት አቅርቦትና ፍላጎት ችግርን የሚፈታ በቂ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ሊያቀርብ የሚችል የንግድ ድርጅት ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱም በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review