የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ እና የበጀት አመቱን ማጠቃለያ ጉባኤ በአድዋ ድል መታሰቢያ እያካሄደ ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባቀረቡት የ2017 በጀት አመት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት፣ የቀዳማይ ልጅነትን ጨምሮ በከተማ አስተዳደሩ በተሰሩ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን አብራርተዋል።
አዲስ አበባ ህፃናትን ለማሳደግ የምትመች ምርጧ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ የተሰነቀውን ራዕይ ለማሳካት፣ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ስኬታማ አፈጻጸም አሳይቷል ብለዋል።
ከንቲባዋ አያይዘውም የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም በከተማዋ ከሚገኙ 1.3 ሚሊየን ገደማ ህጻናት መካከል በዋናነት 330 ሺህ የሚጠጉ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ህጻናት ለመድረስ ያለሙ አምስት አንኳር ኢኒሼቲቮችን አቅደን ስንተገብር ቆይተናልም ነው ያሉት።

ከተማ አስተዳደሩ ለወላጆች እና ለአሳዳጊዎች የምክር እና የሙያ አገልግሎት የሚሰጡ 5 ሺህ ሰራተኞችን በማሰማራት ከ4 ሺህ በላይ የመኖሪያ ብሎኮች ለሚገኙ ከ487 ሺህ በላይ ወላጆች እና አሳዳጊዎች በወር ሁለት ጊዜ የቤት ለቤት የምክር አገልግሎት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ በወጠነው ሰው ተኮር የልማት ስራዎች ከ11 ሺህ በላይ አነስተኛ ገቢ ላላቸው እና ለእድገት ውስንነት ተጋላጭ ለሆኑ ነፍሰ ጡር እና ለሚያጠቡ እናቶች እንዲሁም ከ3 ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት የቀጥታ አልሚ ምግብ ድጋፍ ማድረጉንም ገልጸዋል።
ስራውን አጠናክሮ ለመቀጠል በዚህ በጀት አመትም ከ 5ዐዐ ሚሊየን በላይ በጀት ለአልሚ ምግብ መበጀቱንም ከንቲባዋ በሪፖርታቸው አንስተዋል፡፡
በአጠቃላይ በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም የተከናወኑ ስራዎች ከልጆች እድገት አንጻር የተመዘገቡት ውጤቶች ገለልተኛ በሆኑ ተቋማት ጥናት ይፋ መደረጉንም አብራርተዋል፡፡
በወርቅነህ አቢዮ