የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛና የበጀት አመቱን ማጠቃለያ ጉባኤ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
የከተማ አስተዳደሩን የ2017 በጀት አመት እቅድ አፈፃፀም ለምክር ቤት አባላት ያቀረቡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በበጀት አመቱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤት አቅርቦትን ለማሟላት ከተማ አስተዳደሩ ተግቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በመዲናዋ በቤት ግንባታ በርካታ ባለድርሻ አካለት መሳተፋቸውን የገለጹት ከንቲባዋ፣ በአጠቃላይ በ2017 በጀት አመት ብቻ 55ሺ 729 ቤቶች ተገንብተው ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ መቻሉን አርብራርተዋል።

በበጀት አመቱ በህገ-ወጦች የተያዙ 453 የመንግስት ቤቶች እና 212 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በድምሩ 665 ቤቶችን በማስለቀቅ አገልግሎቱ ለሚገባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ማስተላለፍ መቻሉንም ከንቲባ አዳነች በሪፖርታቸው ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ተወስዶ ከነበረ ከ54 ቢሊዮን ብር የቦንድ ግዥ እዳ ውስጥ 22 ቢሊዮኑን በመክፈል፣ ከተማ አስተዳደሩ ያለበትን የብድር መጠን ወደ 32 ነጥብ 72 ቢሊዮን ብር ዝቅ ማድረግ መቻሉን ከንቲባ አዳነች በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች የቤት አቅርቦትን በተመለከተ በርካታ ተስፋ ሰጪ ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸው፣ በቀጣይም የቤት አቅርቦት ፍላጐትን ሙሉ ለሙሉ ለማጣጣም ሰፊ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል።
በወርቅነው ዐቢዮ