የመዲናዋን የውሃ አቅርቦት እና የፍሳሽ አገልግሎት ለማሳደግ በበጀት አመቱ 18 ቢሊዮን ብር ተበጅቶ ሲሰራ እንደነበር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ

You are currently viewing የመዲናዋን የውሃ አቅርቦት እና የፍሳሽ አገልግሎት ለማሳደግ በበጀት አመቱ 18 ቢሊዮን ብር ተበጅቶ ሲሰራ እንደነበር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ

AMN-ሐምሌ 4/2017 ዓ.ም

3ኛው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛው የበጀት ዓመት ማጠቃለያ ጉባዔ ላይ የከተማ አስተዳደሩን የ2017 ዓ.ም የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በበጀት አመቱ የመዲናዋን የውሃ አቅርቦት እና የፍሳሽ አገልግሎት ለማሳደግ የተሰሩ ተግባራትን ለምክር ቤቱ አባላት አቅርበዋል፡፡

በመዲናዋ ያለውን የውሃ አቅርቦት እና የፍሳሽ አገልግሎት ለማሳደግ ከመንግስት እና ከብድር በተመደበ 18 ቢሊየን ብር በጀት የተለያዩ ፕሮጀክቶች ሲተገበሩ መቆየታቸው በሪፖርቱ ተነስቷል፡፡

በበጀት ዓመቱ የውኃ አቅርቦቱን ለማሳደግ በተሰራው ስራ 81 በመቶው የተሳካ ሲሆን፣ በዚህም 650ሺ የሚደርሱ የመዲናዋ ነዋሪዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋ ከንቲባ አዳነች በሪፖርታቸው፡፡

በበጀት አመቱ በቀን 100ሺ ሜትር ኩብ ውኃ ማምረት የሚያስችሉ የ18 ጉድጓዶች ቁፋሮ የተጠናቀቀ ሲሆን ወደ ስርጭት ለማስገባት የሚያስችል የተቋራጮች ቅጥርም እየተፈፀመ እንደሚገኝ ከንቲባዋ በሪፖርታቸው አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ከከርሰ ምድር ውሃ ልማት ጋር በተያያዘ በቀን 73 ሺ ሜትር ኩብ ውኃ ማምረት የሚያስችለው የገርቢ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት መጀመሩንም ከንቲባዋ ጠቁመዋል፡፡

የዘመናዊ ፍሳሽ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግም በቀን 30ሺ ሜትር ኩብ ፍሳሽ የማጣራት አቅም ያለው እና 240 ሺ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የቦሌ አራብሳ ኮንደሚኒየም የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ የግንባታ ሥራ ተጠናቆ ወደ አገልግሎት መስጠት መጀመሩንም ከንቲባ አዳነች በሪፖርታቸው አንስተዋል፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review