የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ እና የበጀት ዓመቱን ማጠቃለያ ጉባኤ እያካሄደ ይገኛል፡፡
አስፈጸሚ አካለትም ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ላይ የሚገኙ ሲሆን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋዉ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ከጸጥታ ስራዎችና ወንጀልን ከመከላከል አንጻር ህዝቡን ፤ የሰላም ሰራዊቱን ፤ ደንብ አስከባሪዎችን ፤ የፌደራል ጸጥታና ደህንነት አካላትን በማሳተፍ በተሰራዉ ስራ አበረታች ዉጤት መገኘቱን አንስተዋል፡፡
ከስትራቴጂክ ግብ አንጻር ወንጀልን 43 ከመቶ መቀነስ መቻሉን ያነሱት ኮሚሽነሩ በ2016 ዓ.ም ከተፈጸመዉ ወንጀል አንጸር ሲታይ 18 በመቶ ወንጀልን ቀንሰናል ብለዋል፡፡
ወንጀልን ለመከላከል በተሰሩ ስራዎች ተጠርጣሪዎችን ጨምሮ ገንዘቦች፤ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችና የተለያዩ ኢግዚቢቶች በበጀት አመቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸዉን አንስተዋል፡፡
በመዲናዋ የጦር መሳረያን በመጠቀም ጭምር በተደራጀ መንገድ ዘረፋና የተለያዩ ወንጀሎችን ሲፈጸሙ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን በክትትልና በኦፕሬሽን በቁጥጥር ስር በማዋል በህግ እንዲጠየቁ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ወንጀልን ከማጣራት ረገድ ዉጤታማ ስራ መከናወኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ ሌሎች ወንጀሎችን ከመከላከል ረገድም አበረታች ለዉጥ በገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች የገንዘብና የጦር መሳሪያ ዝዉዉሮችን ጨምሮ በተለያዩ ወንጀሎች ላይ የተሳተፉ አካላትን ለጸጥታና ደህንነት አካላት ጥቆማ በመስጠት አበረታች ተሳትፎ ማድረጋቸዉንም ገልጸዋል፡፡
የኢኮኖሚ አሻጥሮችንና ኮንትሮባንድን ከመከላከልና መቆጣጠር ረገድ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በተሰራዉ ቅንጅታዊ ስራ ለዉጥ መታየቱን ጠቁመዋል፡፡
የተለያዩ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ወንጀለኞችን በቀላሉ የመቆጣጠር አቅም ላይ ደርሰናል ያሉት ኮሚሽነሩ ወንጀል በመከላከል ረገድ ለተገኘዉ ዉጤት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አብራርተዋል፡፡