የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ፤ገቢና ልማት

You are currently viewing የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ፤ገቢና ልማት

የከተማዋ ገቢ እያደገ በመጣበት ልክ ልማቷም እየተፋጠነ መሆኑ ተገልጿል

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚሰበስበው ገቢ ከፍተኛ ዕድገት እያሳየ ይገኛል፤ ከዓመት ዓመት በሰፊ ልዩነት ሲጨምርም ይስተዋላል፡፡ ለአብነት በ2013 ዓ.ም 42 ቢሊዮን ብር፣ በ2014 ዓ.ም ከተማዋ 55 ነጥብ 77 ቢሊዮን ብር፣ በ2015 ዓ.ም 108 ቢሊዮን ብር ሰብስባለች። በጀቷም በዚያው ልክ እየጨመረና ህዝባዊ ጠቀሜታ ያላቸው ግዙፍ የልማት ስራዎችን የመከወን ዕድል ተፈጥሯል፡፡

በ3ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉበዔ ላይ በአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የቀረበው ሪፖርትም እንደሚያሳየው በ2017 በጀት ዓመት 241‌ ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ 233 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 96 ነጥብ 5 በመቶ ማሳካት ተችሏል። ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት 83 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው እንደማለት ነው፡፡   

ወደ ኋላ መለስ ብለን የመዲናዋን የበጀት ዕድገት ለማሳያነት ብንመለከት በ2013 ዓ.ም 61 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ ባለፉት ዓመታት በአራት እጥፍ ገደማ ለማደግ የፈጀበት አምስት ዓመት ብቻ መሆኑን እንመለከታለን። የ2018 በጀት ዓመትም ለከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ 350 ቢሊዮን ብር ቀርቦ ፀድቋል። በዋናነት ድህነት ቅነሳ ላይ ትኩረት ያደርጋል የተባለለት ይህ በጀት በተጨማሪም ለዘላቂ ልማት እና የሥራ ዕድል ለሚፈጥሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያነት እንደሚውል ተገልጿል። ለ2018 የተዘጋጀው በጀት ከ2017ቱ በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ108 ነጥብ 11 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው።

ከተማዋ በኢትዮጵያ ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት ከ50 በመቶ በላይ ድርሻ ያላት፤ በራሷ ገቢ የምትተዳደር፤ ስማርት ሲቲ በመሆን ሂደት ውስጥ ያለች እንደመሆኗ ዓመታዊ ገቢዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ ያለው አንድምታ ምንድን ነው? በመዲናዋ እየተከናወኑ ካሉ የልማት ስራዎች አንጻር ምን ትርጉም አለው? በቀጣይ ዓመታትስ የከተማዋን የበጀት አቅም የበለጠ ለማሳደግ ምን መሰራት ይኖርበታል የሚሉና መሰል ጉዳዮችን መፈተሽ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚገልፁት ከሆነ ገቢ ለአንድ ሀገር ህልውና መሰረት ነው፡፡ በተለይ ከሀገር ውስጥ የገቢ ምንጭ የሚሰበሰብ ገቢ አስተማማኝ ልማትን የማረጋገጥ ዕድል ይሰጣል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ሙያዊ ማብራሪያ የሰጡት በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር ዘካሪያስ ሚኖታ (ዶ/ር)፣ ልማትና ገቢ የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ስለመሆናቸው ያስረዳሉ፡፡ ጠንካራ የበጀት ስርዓት ሲኖር ሰፋፊ የልማት ስራ ይኖራል ልማቱ ሲያድግ ደግሞ በጀት የመሰብሰብ አቅምም እየጎለበት ይመጣል፡፡ የከተማዋም በጀት በየዓመቱ እያደገ የመምጣቱ አንደኛው ሚስጥር ይኽው ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያሳየው ከተማዋ ከታክስና ከተለያዩ የገቢ ምንጮች የምትሰበስበው ገቢ ከዓመት ወደ ዓመት ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ መጥቷል፡፡ ለዚህም ለዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱ የራሱ ድርሻ እንዳለውና ፍሬያማ እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡ በሪፖርቱ መሠረት የቱሪዝም ዘርፉን ብቻ ነጥለን እንመልከት፡፡

መዲናዋን የቱሪዝም መዳረሻ፣ የኮንቬንሽን እና ኤግዚቢሽን ማዕከል ከማድረግ ረገድ አበረታች ውጤት መመዝገቡ በሪፖርቱ ተገልጿል። በበጀት ዓመቱም በተካሄዱ ከ150 በላይ ኮንፍረንሶች፣ ኤግዚቢሽኖች እና ኤክስፖዎች ላይ ከተሳተፉ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች በከተማ ደረጃ የተሻለ ገቢ ማግኘት መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አስረድተዋል።

ለዚህ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት፣ የቱሪዝም መዳረሻዎች፣ የመንገድና የመሰረተ ልማት ስራዎች በየዓመቱ እያደገ ላለው የበጀት መጠን ድርሻቸው ወሳኝ ነው፡፡ የልማት ስራዎቹ መሰራታቸው ብቻም ሳይሆን በጥራት ተሰርተው በፍጥነት ወደ ስራ ስለሚገቡ ኢኮኖሚያዊ አበርክቷቸው የላቀ ነው የሚለውም የምጣኔ ሀብት መምህሩ አስተያየት ነው፡፡

እንደ መምህር ዘካሪያስ (ዶ/ር)፣ አስተያየት ከሆነ አሁንም ቢሆን ከተማዋ የሚገባትን የልማት ስራዎች እንድታገኝና በዓመቱ የገቢ ዕቅዷን ለማሳካት ከታክስና ከተለያዩ ምንጮች ገቢ ለማሳደግ የተለያዩ አማራጮችን መፈተሽ ያስፈልጋል። የመሰረተ-ልማት ግንባታ፣ ሰብዓዊ ልማትና የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማቅረብ የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን ከታክስና ከተለያዩ ምንጮች ገቢን መፈለግ የግድ ነው፡፡ አዲስ አበባ በርካታ አምራች ድርጅቶች፣ የፋይናንስ ተቋማትና ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚከናወንባት ከተማ በመሆኗ ሰፊ ገቢ የመሰብሰብ አቅም እንዳላትም መገመት አያዳግትም።

የተቀመጠውን የበጀት እቅድ ለማሳካት የገቢ አሰባሰብ ሰርዓትን የበለጠ ማዘመን እንደሚገባ አንስተዋል። ይህ ሲሆን ከተማዋ የጀመረቻቸውን ሜጋ ኘሮጀክቶች ለማጠናቀቅ እንደ የቤት ልማት ፕሮግራሞችን፣ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት፣ የሌማት ትሩፋትና የከተማ ግብርናን ማስፋት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ይደረጋል በማለት መምህር ዘካሪያስ (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡

ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም በተካሄደው የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 42ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት ከተሞች 60 በመቶ ድርሻ እንዳላቸውና የአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ከ50 በመቶ በላይ ድርሻ እንዳላት ተናግረው ነበር፡፡

ከ50 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያለው በአዲስ አበባ ከተማ እንደሆነም አውስተው፣ አዲስ አበባ ላይ ካልተሠራ ይህን ኢኮኖሚ መጠቀም እንደማይቻል ገልጸዋል። “ከተማን ማነቃነቅ አጠቃላይ ሀብታችንን ማነቃነቅ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ እስከ አሁን አዲስ አበባ ላይ በተሠራው ሥራ ምንም ብድር እንዳልተወሰደም ጠቁመዋል። ይህም የከተማዋ ዓመታዊ በጀት በየጊዜው እያደገ ስለመምጣቱ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡

እዚህ ጋር ታዲያ ለማሳያነት ይረዳ ዘንድ የተወሰኑ ዓመታትን የመዲናዋን የበጀት አሐዛዊ ቁጥሮችን እናክል፡፡ ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ በጀት፤ ከ2014 እስከ 2018 ባሉት አምስት ዓመታት ውስጥ በ395 ነጥብ 25 በመቶ አድጓል። ይህም በ2014 ዓ.ም 70 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የነበረው የከተማ አስተዳደሩ በጀት በአምስት ዓመት ውስጥ በአምስት እጥፍ ገደማ እንዳደገ ያመላክታል።

ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በምክር ቤት ቀርበው ባቀረቡት ሪፖርት የተጀመሩ ተስፋ ሰጪና አበረታች ውጤቶችን በማስቀጠል በቀጣይ በትኩረት ይሰራባቸዋል ያሏቸውን ጉዳዮች አብራርተዋል፡፡

ከንቲባዋ በማብራሪያቸው የተጀመረውን ተቋማዊ ሪፎርም አጠናክሮ ማስቀጠል፣ የገቢ አሰባሰብ ሰርዓትን የበለጠ በማዘመን፣ የገቢ እቅድን ማሳካት፣ እንዲሁም የቤት ልማት ፕሮግራሞችን በግል ዘርፉ፣ በሕብረት ሥራ ማኅበራት፣ በመንግስትና በግል የአጋርነት ፕሮግራም በስፋት ተግባራዊ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

አክለውም የውሃ አቅርቦትና ሌሎች የተጀመሩ ሜጋ ኘሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እንደሚሰራና የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት፣ የሌማት ትሩፋትና የከተማ ግብርናን ማስፋት፣ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ይደረጋል ብለዋል። የሥራ ዕድል ፈጠራ ስራችን በተለይም የወጣቶች የሥራ አድል እና አምራች ኢንዱስትሪን የማስፋትና ተወዳዳሪነቱን የማሳደግ ስራ በልዩ ትኩረት ይከናወናል ሲሉም አክለዋል፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review