በደን ልማት ወሳኙ ምዕራፍ

You are currently viewing በደን ልማት ወሳኙ ምዕራፍ

ምድር በአስፈሪ ሁኔታ እየሞቀች ነው የሚለው መረጃ ከተሰማ ዓመታት ነጉደዋል፡፡ ምድር በአንድ ጎኗ በሙቀት ሳቢያ በሚመጣ የበረዶ መቅለጥ እና ጎርፍ ትጠቃለች፤ በሌላ ጎኗ ደግሞ በሰደድ እሳት እየተለበለበች ትገኛለች፡፡ ጎርፍ፣ ከባድ ሙቀትና አውሎንፋስ እያደረሱባት ያለው ጉዳት የዓለም መገናኛ ብዙሃንን የአየር ሰዓት ካጨናነቀም ሰነባብቷል፡፡

በአሜሪካ በደቡብ ምሥራቃዊ አቅጣጫ በምትገኘው ሉዚያና ግዛት አንስቶ በሩቅ ምሥራቋ ጃፓን ድረስ አውሎ ንፋስ እያደረሰ ያለው አደጋ ለዚህ አስረጅ ነው፡፡ ገፅታው ይለያይ እንጂ በአዳጊ ሀገራትም ላይ በርካታ ችግሮችን እያስከተለ ይገኛል። 

በቅርብ ዓመታት ልዩነት እየተመላለሱ ምድርን የሚጎበኙ የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያታቸው ደግሞ በሰው ልጆች የሚተገበሩ የደን ጭፍጨፋዎች እና የበካይ ጋዝ ልቀቶች ስለመሆናቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ከመግለፅ ቦዝነው አያውቁም፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋነኛ መወያያ አጀንዳ ሆኖ በድርጅቱ ጠረጴዛ ላይ የተገኘውም ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ገደማ ነበር፡፡ 

የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ሀገራት ለስኬታማ የደን ልማት ስራ በቂ በጀትና ጊዜ መድበው እየሰሩ ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል ደቡብ ኮሪያ፣ ብራዚል እና ካናዳ በዓለም ላይ ትልቅ የደን ሽፋን ካላቸው ሀገራት በቀዳሚነት ተጠቃሽ ናቸው። በዘላቂ የደን አስተዳደር ስራቸው በተደጋጋሚ ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኙትን እንደ ስዊድን እና ፊንላንድ ያሉ የአውሮፓ ሀገራትን ሳንዘነጋ ማለት ነው። በተጨማሪም እንደ አውስትራሊያ እና ቻይና ያሉትም ከፍተኛ የደን መልሶ ማልማት ስኬት ያሳዩ ሀገራት ናቸው። ከአፍሪካም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደ ኢትዮጵያና ጋቦን ያሉ ሀገራት ዘላቂነት ያለው የደን አስተዳደር ስርዓት በመዘርጋት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የደን ልማት ስራን በጠንካራ ፖሊሲ ማገዝ፣ ወጥነት ያለውና ያልተቆራረጠ ስራ መስራት እና ለደን ልማት ስራ ወሳኝ ምዕራፍ ለሆነው የቅድመ ዝግጅት ስራ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ በፔንስልቬንያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የደን ልማት ባለሙያ ቲያና ዱፖንት ያስረዳሉ። እርሳቸው እንደሚሉት ደግሞ የእነዚህ ሀገራት የስኬት ሚስጥር ይኽው ነው፡፡

ሀገራቱ የተሳካ የደን ልማት ስራ እንዴት ሊያከናውኑ ቻሉ? ለሚለው ጥያቄ ደግሞ ደቡብ ኮሪያን እንደምሳሌ ወስደው በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉት በጆርጂያ ዩኒቨርሲቲ የሰብል እና የአፈር ሳይንስ ክፍል ተመራማሪው ታይለር ዲንማን ተጨማሪ ማብራሪያ አላቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ደቡብ ኮሪያውያን የደን ልማት ስራን የሚያከናውኑት በጠንካራ ፖሊሲና ሳይንሳዊ ምርምር ታግዘው ስለመሆኑ ያስረዳሉ፡፡

በእርግጥም ተመራማሪው ታይለር ዲንማን እንደፃፉት ከሆነ፣ ደቡብ ኮሪያ የኢኮኖሚ ልማትን ከአረንጓዴ ልማት ጋር በማጣጣምና ሀገራዊ አጀንዳ በማድረግ ፈር ቀዳጅ ሀገር ነች። እ.ኤ.አ በ2008 ኮሪያ ‘ዝቅተኛ ካርቦን፣ አረንጓዴ እድገት’ በሚል መርህ ከመካከለኛ እስከ የረጅም ጊዜ የልማት ራዕይ (ማለትም ከ2009 እስከ 2050) ይፋ አድርገው ነው ወደስራ የገቡት።

የደን ልማት ሂደቱ ከችግኝ ተከላ ጀምሮ ያሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እንዲከናወኑ ጠንካራ አሰራሮችን የዘረጋችው ደቡብ ኮሪያ የተሻለ ውጤት አግኝታበታለች፡፡ በተለይም ችግኞች በቂ ውሃ፣ ተገቢውን ብርሃን እና ሙቀት እንዲያገኙ በማድረግና ጥራት ያለው አፈር በማዘጋጀት ለተሻለ ውጤት መብቃታቸውን የአፈር ሳይንስ ተመራማሪው ታይለር ዲንማን ያብራራሉ፡፡

ችግኝ ማፍላትና ጉድጓድ ማዘጋጀት በፅድቀት ምጣኔ ላይ ያላቸው ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑን የሚጠቅሱት ተመራማሪው፣ ለኮሪያውያኑ የደን ልማት የስኬት ሚስጥርም እነዚህን ጉዳዮች ሳያዛንፉ መስራታቸው እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

የደን ​​ስነ ምህዳር አስተዳደር ባለሙያ የሆኑት ቻይናዊው ሹ ዜንግ ታንግ በበኩላቸው፣ የችግኝ ተከላ ስራ ውጤታማ እንዲሆን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ወሳኝ ናቸው ይላሉ። ሊደረጉ የሚገባቸውን ዝግጅቶች ሲያብራሩም ችግኝ ከማዘጋጀት ጀምሮ ተከላና የእንክብካቤ ስራው ሳይንሳዊ እውቀትን መሰረት አድርጎ ካልተከናወነ የፅድቀት መጠኑ አነስተኛ ነው፡፡ በመሆኑም በችግኝ ጣቢያዎች የሚፈሉ የዛፍ ዘሮችን በጥንቃቄ መምረጥ፤ የሚተከሉት ችግኞች ለምን ዓላማ የሚውሉ ናቸው? የእንጨት ውጤቶችን ለማምረት፣ አካባቢን ለማስዋብ፣ የአፈርና ውሃ መሸርሸርን ለመከላከል ወይስ ለሌላ? የሚለውን ጉዳይ ማወቅና መለየት ይገባል ይላሉ፡፡

ባለሙያዎቹ እንደሚያስረዱትም ለተከላ የሚዘጋጀው ችግኝ በአግባቡ እንክብካቤ ተደርጎለት ዝግጁ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ቁመታቸው ከ40 እስከ 50 ሴንቲ ሜትር የደረሱ መሆን አለባቸው። ለተከላ ያልደረሱ ከሆኑ አቆይቶ በቀጣይ ዓመት እንዲተከሉ ማድረግ ይገባል። የጉድጓድ ቁፋሮው ቢቻል ከአንድ ወር በፊት ካልሆነም ከተከላው አሥራ አምስት ቀን ቀደም ብሎ መጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡ ይህም የችግኝ መትከያ ጉድጓዱ በቂ እርጥበት እንዲይዝ ይረዳዋል፡፡ የችግኝ መትከያ ጉድጓድ ጥልቀቱም ከ3ዐ እስከ 4ዐ ሴንቲ ሜትር ቢሆን ይመረጣል፡፡ ጉድጓድ በሚቆፈርበት ጊዜ ከጉድጓዱ ተቆፍሮ የሚወጣውን የላይኛው አፈር ሳይበታተን ከጉድጓዱ ጎን መከመር ይኖርበታል፡፡

በችግኝ ጣቢያ የተዘጋጀ ችግኝ በሙሉ ለተከላ ብቁ ነው ማለት አይደለም የሚሉት ደግሞ በፔንስልቬንያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የደን ልማት ባለሙያ ቲያና ዱፖንት ናቸው፡፡ ባለሙያው ጉዳዩን ሲያብራሩም ለተከላ ያልደረሰ ችግኝ ቢተከል ከችግኝ ጣቢያ ውጭ ያለውን አካባቢና አረም መቋቋም ስለማይችል የጽድቀት መጠኑ አነስተኛ ይሆናል፡፡ ለተከላ የሚመረጥ ችግኝ የግንዱ ቁመት ከስሩ ቁመት በአማካይ ሁለት እጥፍ መብለጥና ጠንካራ ሊሆን ይገባል፡፡ ችግኙ በፈንገስ ወይንም በነፍሳት በአጠቃላይ በበሽታ ያልተጠቃና ጤናማ ሊሆን ይገባል፡፡ የተወላገደ ግንድ ያለው መጠኑ ከሚገባው በላይ ትንሽ ወይም ትልቅ የሆነ ችግኝ፣ ቅጠሉ ወደ ቢጫነት የተለወጠ ችግኝ ለተከላ ተገቢ አለመሆኑንና ቢተከልም የመጽደቅ ዕድሉ በጣም አነስተኛ እንደሚሆን አስፍረዋል፡፡

የደን ልማት ባለሙያው ቲያና አክለውም የችግኝ ተከላ ከመካሄዱ በፊት በቅድሚያ ጉድጓዱ ውስጥ የገቡ ባዕድ ነገሮችንና ውሃ ማውጣት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ችግኙ ጉድጓድ ውስጥ ከመግባቱ በፊት ተለይቶ የተቀመጠውን የላይኛው አፈር እስከ ጉድጓድ ግማሽ (15 ሴንቲ ሜትር) ድረስ መመለስ ያስፈልጋል፣ ይህም የሚደረገው የመትከያው ጉድጓድ ከሚፈለገው በላይ ጥልቀት ያለው ከሆነ ችግኙ እንዳይቀበር ለማድረግና ጥልቀቱን ለማስተካከል ስለሚረዳ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ባለሙያዎቹ እንደሚገልፁት የደን ልማት ሰራ ውጤታማ እንዲሆን ቢያንስ ሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች ከግንዛቤ መግባት አለባቸው፡፡ እነዚህም ስራውን በጠንካራ ፖሊሲና ህግ ማገዝ፣ ወጥና ተከታታይነት ያለው ስራ መስራት እንዲሁም ሳይንሳዊ የሆነ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን መስራት የግድ ይላል፡፡ ይህ ካልሆነ ለበርካቶች ሕይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ምክንያት የሆነው ወቅታዊው የዓለም ፈተና የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የሚቻል አይመስልም፡፡

የጉዳዩን አሳሳቢነት ለመግለጽ ይረዳን ዘንድ አንዳንድ መረጃዎችን አቅርበን ጽሑፋችንን እንቋጭ፡፡ ዓለማችን በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከነበረችበት የሙቀት መጠን አሁን በ1 ነጥብ 2 ድግሪ ሴልሺዬስ ጨምራለች። ወደ አየር ንብረት የሚለቀቀው የካርቦን ዳይ ኦክሳይድ መጠን ደግሞ 50 በመቶ አድጓል። እንደ ዘርፉ ባለሙያዎች አስተያየት ከሆነ ደግሞ የምድራችን ሙቀት መጠን እንደ እ.ኤ.አ በ2100 ባለበት 1 ነጥብ 5 ድግሪ ሴልሺዬስ መቆየት አለበት። ነገር ግን አሁን ላይ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ካልተቻለ የምድራችን ሙቀት መጠን በያዝነው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ወደ 2 ድግሪ ሴልሺዬስ ከፍ ሊል ይችላል።

ባለሙያዎቹ አያይዘውም እንደሚገልጹት ችግሩን ለመግታት እርምጃ ካልተወሰደ እስከ 550 የሚደርሱ የእንሰሳት ዝርያዎች በያዝነው ክፍለ ዘመን ሊጠፉ ይችላሉ። አስጊው ነገር ግን ይህ ብቻ አይደለም ይላሉ ሳይንቲስቶች። የሙቀት መጠኑ አሀዝ ወደ 4 ዲግሪ ሴልሺዬስ ከፍ ሊልም እንደሚችልና ይህ ማለት ደግሞ አስከፊ ሙቀት ተከስቶ ሚሊዮኖች በውሃ መጠን መጨመር ምክንያት ከመኖሪያቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ በተለይም እፅዋትና እንስሳት ከምድራችን ሊጠፉ እንደሚችሉም ጭምር እያሳሰቡ ይገኛሉ። ስለዚህ በደን ልማት ስራ ውስጥ ለችግኝ ፅድቀት መጠን ማደግ ወሳኝ በሆነው የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ላይ ማተኮር ተመካሪ ጉዳይ ነው።

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review