“በምክክሩ ሂደት የማደርገውን ተሳትፎ አጠናክሬእቀጥላለሁ”

You are currently viewing “በምክክሩ ሂደት የማደርገውን ተሳትፎ አጠናክሬእቀጥላለሁ”

      የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ብሔራዊ መግባባት እንደሚያስፈልግ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲነሳና ሲጠየቅ ቆይቷል። ብሔራዊ መግባባት ለማምጣት ያለሙ ውይይቶች በተለያዩ ዜጎችና ቡድኖች በጎ ፈቃድ ለማካሄድም ጥረት ተደርጓል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሂደቶች ውጤታማ ያልሆኑ ወይም ባክነው የቀሩ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ የሚቻል ቢሆንም የሂደቶቹ አካታች አለመሆንና በስልጣን ያለው መንግስት ፈቃደኝነት ውስን መሆን እንደሚጠቀሱ በ1960ዎቹ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የተሳተፉት፣ በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሀሳባቸውን በማካፈል የሚታወቁት ደስታ መብራቱ (ፕሮፌሰር) “ምህዳራዊ አስተሳሰብ ለዘላቂ መፍትሔ” በሚል ርዕስ ከፃፉት መፅሐፍ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህንን እውነታም ምሁራን፣ የሲቪክ ማህበራትና መንግስትን ጨምሮ ይጋሩታል፡፡

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት ለሰው ህይወት መጥፋትና ለንብረት ውድመት ምክንያት የሆኑ ለዘመናት እየተንከባለሉ የመጡ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት እንዲቻል ተነሳሽነቱን ወስዷል፡፡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ለአለመግባባትና ልዩነት ምክንያት የሆኑ መሰረታዊ ጉዳዮችን በመለየትና ምክክር በማድረግ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እየተሰራ ይገኛል፡፡ በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ እንደሰፈረው፣ ሀገራዊ ምክክሩና የምክክሩ ሂደት በሚከናወንበት ወቅት ከግምት ውስጥ ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል አካታችነትና አሳታፊነት ይጠቀሳል፡፡

በግጭት አፈታትና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ በአንድ ሀገር ላይ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን ሁሉ ማሳተፍ ለውጤታማነት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።  በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ሀገራዊ ምክክር ሂደትም ህዝብን የሚወክሉ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ድምፃቸው እንዲሰማ፣ አጀንዳቸውን ለማካተት ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል አካል ጉዳተኞች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞችን ቁጥር ለማወቅ የሚያስችል በቅርብ የተሰራ ጥናት ማግኘት ባይቻልም፤ የዓለም ባንክና የዓለም ጤና ድርጅት በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2011 በጋራ ያወጡት መረጃ እንደሚያሳየው፣ የአካል ጉዳተኞች ቁጥር ከጠቅላላው ህዝብ ውስጥ የ17 ነጥብ 6 በመቶ ወይም ወደ 20 ሚሊዮን ይገመታል፡፡ እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች በባህል፣ በአመለካከትና ተገቢውን ትኩረት ባለማግኘት አቅም እያላቸውና እየቻሉ፣ ምቹ ሁኔታዎች ባለመመቻቸቱ፣ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በአግባቡ እንዲሳተፉ ባለመደረጉ ተጎጂ ሆነው ቆይተዋል፡፡ ሀገርም በትክክል ማግኘት ያለባትን ጥቅም ሳታገኝ እንድትቆይ አድርጓል ማለት ይቻላል፡፡

የሰላም እጦት ሁሉንም ማህበረሰብ ይጎዳል፡፡ በተለይ  ሰላም ባለመኖሩ በይበልጥ ለከፋ ችግር ተጋላጭ የሚሆኑት አካል ጉዳተኞ ናቸው ይላሉ በቅርቡ በፌዴራል ደረጃ በተካሄደው የባለድርሻ አካላት አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት የተሳተፉት፣ የኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ማህበር ፕሬዝዳንትና የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አበራ ረታ፡፡

ሰላምን ለማስፈን የሚደረግ ማንኛውም ጥረት አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ ሀገራዊ ምክክሩም ዘላቂ ሰላምን በማምጣት አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ስራውን በሙሉ ልብ እንደሚደግፉት ይናገራሉ፡፡

በተለይ በፌዴራል ደረጃ የተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ሰላም ሰላም በሚሸት፣ ዜጎች በሀገራቸው እምነትና ተስፋ እንዲኖራቸው ባደረገ መልኩ ነው፡፡ ከየትኛውም አካል የሚነሱ አጀንዳዎች ሳይጨፈለቁ ለማካተት ጥረት ተደርጓል፡፡ ከቀረቡት አጀንዳዎች በይዘት የሚመሳሰሉትን ወደ አንድ በማምጣት የፌዴራል ባለድርሻዎች አጀንዳ ተብሎ እንዲያዝ ተደርጎል፡፡ ከአካል ጉዳተኛ የህብረተሰብ ክፍሎች የቀረቡ አጀንዳዎች መያዛቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ሌላኛው ሀሳባቸውን ያጋሩን መቶ አለቃ በቀለ ጎንፋ ይባላሉ፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰራዊት አባል ናቸው። የሰላም እጦትና ግጭት ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍል በተጨባጭ ከሚያውቁት መካከል ናቸው። ምክንያቱም በጦርነት ምክንያት ጓዶቻቸውን አጥተዋል፡፡ እርሳቸውም በምስራቅ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር በተደረገው ጦርነት አንድ እግራቸውን አጥተዋል፡፡ የሰላም እጦት፣ ግጭት፣ ጦርነት ዜጎችን ለአካል ጉዳትና ህልፈት እንዲሁም የንብረት ውድመት የሚዳርግ፣ የሀገርን እድገት ወደኋላ የሚጎትት በመሆኑ ለማንም የሚበጅ አይደለም ይላሉ፡፡

ግጭትና አለመረጋጋት ባለባቸው አካባቢዎች በተለይ አካል ጉዳተኞች ተጎጂ ናቸው፡፡ በነጻነት ሰርተውና ተንቀሳቅሰው መኖር፣ ከግጭት ማምለጥ አይችሉም፡፡ ጉዳቱ ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለቤተሰብና ለወገንም ይተርፋል፡፡

ከዚህ አኳያ በሀገራችን ሰላምን ለማምጣት የሚደረጉ ጥረቶችን ሁሉ እንደሚደግፉ መቶ አለቃ በቀለ ያነሳሉ። ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የተያዘው ሀገራዊ ምክክር ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም አካል ለሰላም እንቅፋት ናቸው የሚላቸውን መነሻ ምክንያቶች በመለየት ለኮሚሽኑ አጀንዳውን ማቅረብ ይገባዋል። በምክክሩም ለልዩነትና ግጭት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን በደንብ ለይቶ በማውጣት፣ በሰከነ መንገድ በመወያየት መግባባት ላይ መድረስ እንደሚቻል መቶ አለቃ በቀለ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን የኮሙኒኬሽን ክፍል ኃላፊ አቶ ታደሰ መሸሻ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ማረጋገጥ አካል ጉዳተኞች አጥብቀው የሚሹት ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም አካል ጉዳተኞች ባለባቸው የአካል ጉዳት ሮጦ ማምለጥ፣ መረጃ አግኝቶ ራስን መጠበቅና መከላከል ስለሚያዳግታቸው ተጎጂዎች ናቸው፡፡

ሌላው የአካል ጉዳተኛ የማህበረሰብ ክፍሎች የአካታችነት ጥያቄ በአግባቡ ባልተመለሰበትና የተለያዩ ችግሮች እየተጋፈጡ በሚኖሩበት ሁኔታ ግጭት መኖር ተጨማሪ አካል ጉዳተኛ እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ከዚህ አንጻር ሀገራዊ ምክክሩ ዘላቂ ሰላምና የተረጋጋ ሀገር ለመፍጠር ሁነኛ መንገድ መሆኑን በመረዳት በሂደቱ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሆነ አቶ ታደሰ ያነሳሉ፡፡ 

አጀንዳ በማሰበሰብ ሂደት በክልልም ሆነ በፌዴራል አካል ጉዳተኛ የህብረተሰብ ክፍሎች ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ማህበራት ፌዴሬሽን ስር ከሚገኙ ማህበራት፣ ባለሙያዎች፣ የአካል ጉዳተኛ መብት ተሟጋች ግለሰቦች ጋር በመመካከርና በማሳተፍ ሶስት ጥቅል አጀንዳዎች ተለይተው በአጀንዳ እንዲያዙ መደረጋቸውን አቶ ታደሰ አስረድተዋል፡፡

አካል ጉዳተኞች እንደማንኛውም ዜጋ ሀገራዊ እንዲሁም ከራሳቸው ከአካል ጉዳተኞች ጋር በተያያዘ በመላ ሀገሪቱ የጋራ አቋም በመያዝ፣ ሁለተናዊ ተሳትፏቸውን የሚያሳድጉ፣ አካታችነትን የሚያረጋግጡ አጀንዳዎችን አቅርበዋል። በሀገራዊ ምክክሩ ከቀረቡና ከተያዙ አጀንዳዎች አንዱ በሀገሪቱ የአካል ጉዳተኞች የፖለቲካ ተሳትፎ ወይም ውክልና የማረጋገጥ ጉዳይ ይገኝበታል፡፡ በክልልና በፌዴራል በሶስቱም የመንግስት አካላት በህግ አውጪው፣ ህግ አስፈፃሚና ተርጓሚ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ጨምሮ በተለያዩ እርከኖች የአካል ጉዳተኛውን ማህበረሰብ የሚወክል መቀመጫ እንዲኖር የሚጠይቅ አጀንዳ ነው፡፡ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው እንደሚገልፁት አካል ጉዳተኞች ውክልናቸው ሲረጋገጥ በራሳቸው ጉዳይ የመወሰን፣ የሚፈጠሩ የፖሊሲ ወይም የህግ ክፍተቶችን የማስተካከል ዕድል ያገኛሉ፡፡

ሌላው የአካል ጉዳተኞችን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ ከህገ መንግስቱ ጀምሮ የወጡ ፖሊሲዎችና የህግ ማዕቀፎች አካል ጉዳተኞችን በተገቢው ሁኔታ ያካተቱ እንዲሆኑ ማሻሻያ እንዲደረግ የተጠየቀበት ጉዳይ ይገኝበታል፡፡ ይህንን አቶ ታደሰ ማሳያ ይሆናል ያሉትን ነጥብ በማንሳት ያስረዳሉ፡፡ ለምሳሌ፡-

በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 41 ንዑስ አንቀፅ 5 ላይ “መንግስት የአካልና የአዕምሮ ጉዳተኞችን፣ አረጋውያንንና ያለወላጅ ወይም ያለአሳዳጊ የቀሩ ህጻናትን ለማቋቋምና ለመርዳት የሀገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም በፈቀደው ደረጃ እንክብካቤ ያደርጋል” በሚል ተቀምጧል፡፡ እዚህ ላይ መንግስት “አቅም በፈቀደ መጠን እንክብካቤ ያደርጋል” የሚለው ለትርጉም ክፍት የሆነ፣ አንዳንድ አካላት የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ ለማካተት “አቅም የለኝም” በሚል ጥረት ባያደርጉ ተጠያቂ የማያደርግና አስገዳጅነት የሌለው በመሆኑ ሊሻሻል ይገባዋል ይላሉ፤ አቶ ታደሰ፡፡

በምክክሩ በአጀንዳ እንዲያዝ የቀረበውና ተቀባይነት ያገኘው ሶስተኛው ጉዳይ በአካል ጉዳተኞች ባለቤትነት የሚመራ የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ የሚመራ ራሱን የቻለ ተቋም እንዲመሰረት የሚጠይቅ ነው፡፡ የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር ነው የሚመራው፡፡ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሰራበት በኤጀንሲ ወይም በሆነ ተቋም ደረጃ የተደራጀ፣ ነፃና የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ ለማስፈፀም፣ የወጡ ፖሊሲዎችንና ህጎችን የሚፈፅም፣ የሚቆጣጠርና የሚከታተል ተቋም እንዲኖር ተፈልጎ እንደሆነ አቶ ታደሰ አስረድተዋል፡፡

በምክክሩ ሂደት ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ጋር በተያያዘ አቶ ታደሰ እንደሚያነሱት መጀመሪያ አካባቢ አንዳንድ የውይይት ቦታዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አልነበሩም፡፡ የምልክት ቋንቋ በበቂ ሁኔታ አለመመደብ ችግር ነበር፡፡ ችግሩን ቀድሞ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማሳወቅና በቅርበት በመነጋገር በሂደት መፍትሔ እየተሰጠው መጥቷል። “በምክክር ሂደቱ አካል ጉዳተኞችን በማካተትና ተደራሽ በማድረግ ያን ያህል የሚባል የጎላ ችግር አልገጠመንም፡፡ በበቂ ሁኔታ ተሳትፎ አድርገናል” ብለዋል፡፡

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ባካሄዳቸው የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረኮች በእያንዳንዱ በክልል ደረጃ እስከ 26 የሚደርሱ አካል ጉዳተኞች አጀንዳ በማሰባሰብ ሂደት ተሳትፈዋል፡፡ በፌዴራል ደረጃ በተካሄደው የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ 21 የሚደርሱ አካል ጉዳተኞች መሳተፋቸውን አቶ ታደሰ ጠቁመዋል፡፡

ኮሚሽኑ ምን እየሰራ ነው?

የግጭት ወይም ጦርነት መኖር ሶስት ችግሮችን ያስከትላል፡፡ በሰዎች ላይ አካላዊ ጉዳት፣ ከፍ ሲል የሕይወት መጥፋትና በአጠቃላይ የአዕምሮ ስብራት ያመጣል የሚሉት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር)፣ ኮሚሽኑ ከመነሻው የተዘነጉ ወይም ልዩ ትኩረት የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ውስጥ ዋና ተሳታፊ እንዲሆኑ መርሁ አድርጎ ነው የተነሳው፡፡ በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉንም አካታችና አሳታፊ እንዲሆን ተቀምጧል፡፡ በዚህም መነሻ አካል ጉዳተኞች ከተወከሉበት ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበር ኮንፌዴሬሽን ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረምና ግንኙነቱን በማጠናከር ከወረዳ እስከ ፌዴራል ድረስ አካል ጉዳተኞች እንዲሳተፉ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን አንስተዋል፡፡

በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱም፤ “አጀንዳዎቻችን ናቸው” የሚሏቸውን በፌዴሬሽናቸው አማካኝነት አቅርበዋል። በቅርቡም መስማት ከተሳናቸው ኢትዮጵያውያን ማህበር የቀረቡ አጀንዳዎችን ኮሚሽኑ ተቀብሏል፡፡ ዓይነ ስውራንና የተለያየ የአካል ጉዳት ያለባቸው በሂደቱ እየተሳተፉ ነው። አንዳንድ “አልተካተትንም” ብለው የሚያስቡ ካሉም አሁንም አጀንዳዎችን እንደሚቀበል ጠቁመዋል፡፡

አካል ጉዳተኞች ያሉባቸው ፈተናዎች ብዙ ናቸው፡፡ በመንገድ፣ በትራንስፖርት፣ በህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና በሌሎችም እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መብት የተሰጣቸው ቢሆንም በትግበራ ላይ ብዙ ችግሮች ይታያሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር ግጭት ሲኖር የበለጠ ተገጂ ከሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል አካል ጉዳተኞች እንደሚጠቀሱ ያነሱት መስፍን (ፕ/ር)፣ በምክክሩ ሂደት ተሳታፊነታቸውን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ቀጣይ ምን ይጠበቃል?

መስፍን (ፕ/ር) እንደሚሉት፣ ምክክር ማለት በድምፅ ብልጫ የሚወሰን ወይም ብዙዎች አስቀድመው ወስነው መጥተው የራሳቸውን አጀንዳ ብቻ የሚያፀድቁበት አይደለም፡፡ ምክክር በሚገባ በመከባበርና በመደማመጥ ተነጋግሮ የጋራ አጀንዳዎች ወደፊት የሚመጡበትና መግባባት ላይ የሚደረስበት ሂደት ነው፡፡ መግባባት ላይ የማይደርስባቸው ጉዳዮች ካሉም ጊዜ በመስጠት በቀጣይነት በህዝበ ውሳኔ ወይም በሌላ መንገድ ወሳኔ እንዲሰጥባቸው ይደረጋል፡፡

መመካከር አጀንዳ መስጠት ብቻ ሳይሆን ስለ አጀንዳው ጥልቅ የሆነ እውቀት መያዝን ይፈልጋል፡፡ እውቀት የሚያስፈልገውም ምክንያታዊ ለመሆን ነው፡፡ ተሳታፊዎች ከወዲሁ በመከባበር፣ በመደማመጥ ተነጋግሮ ወደ መግባባት ለመምጣት ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ መገናኛ ብዙሃን ህዝቦች ተካባብረው ለመደማመጥና ለመነጋገር እንዲችሉ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መስፍን (ፕ/ር) ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አበራም ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን ከእያንዳንዱ ግለሰብ፣ ማህበረሰብና የፖለቲካ ተዋናዮች ሆደ ሰፊነት፣ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገርን ማሰብ ይጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያ የምትገነባው በመቀበል ብቻ ሳይሆን በመስጠትም እንደሆነ መረዳት ይገባል፡፡

ሁላችንም በሰላም ወጥተን፣ ሰርተን፣ በሰላም የምንገባባትና የምንኖርባት ኢትዮጵያን ከፈለግን በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር ይኖርብናል፡፡ በመሰረታዊ ልዩነቶቻችን ላይ መግባባት ከፈጠርን ሌሎች ጥያቄዎችን እየፈቱ መሄዱ ቀላል እንደሆነ አቶ አበራ ያስገነዝባሉ፡፡ 

“ሰላምን ቅድሚያ የምንሰጠው ስለሆነ በየትኛውም አካል ሰላም ለማምጣት የሚደረግ አጀንዳ ላይ እንሳተፋለን፡፡” የሚሉት አቶ ታደሰም፣ በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላምና እድገት ለማረጋገጥ ልዩነቶችን በውይይትና ምክክር መፍታት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን አለበት፡፡ ለሀገራችን ህመም ፈውስ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ ይሆን ዘንድ ሁሉም አካላት ዕድሉን በአግባቡ መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን በምክክሩ ሂደት የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ሀገራዊ ምክክር ኢትዮጵያ ከገባችበት የግጭት አዙሪት ለማውጣት ሁነኛው መንገድ ነው፡፡ የምክክሩ ሂደትና ውጤት በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ሲሆን በተለይ ደግሞ የችግሮች ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ለሆኑ አካል ጉዳተኞች እየተንከባለሉ የመጡ ችግሮችን የሚፈታና ነገን በተስፋ እንዲጠብቁ የሚያደርግ ነው፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review