የመዲናዋ ኪነ-ጥበባዊ መሰናዶዎች

You are currently viewing የመዲናዋ ኪነ-ጥበባዊ መሰናዶዎች

በመዲናችን አዲስ አበባ ባለፉት ቀናት የተለያዩ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶች ለጥበብ አፍቃሪያን ቀርበዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም መሰል ዝግጅቶች ተሰናድተዋል። ከእነዚህ መካከል የፊልም ምርቃት፣ የመጽሐፍ ትመረጃዎች፣ የሙዚቃ ዝግጅቶችና የቴአትር መርሃ ግብር ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳንጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡ 

መጽሐፍት

“ዝይን” የተሰኘ ስብስብ መጽሐፍ ለንባብ ሊበቃነው፡፡ የደራሲ አለማየሁ ገላጋይ የቀደሙ ሦስት የድርሰትሥራዎቹን በአንድ ቅጽ ሆነው ለንባብ እንደሚበቁም አሳውቋል፡፡ ደራሲው በማህበራዊ ትስስር ገጹ ላይ፣ “ዝይንን ዳጎስ ብላ ስመለከት ለመጀመሪያ ጊዜ ‘ለካ ሰርቻለሁ፣ የሀገሬ ሥነጽሑፍ ውስጥ አለሁበት’ የሚል ምስክርነት ለራሴ ተሰማኝ” በማለት አስፍሯል።  “ዝይን” በፍቅርሥም፣ ታለ እና ሐሰተኛው የተሰኙ ቀደምት የልብ ወለድ ድርሰቶቹን በአንድ ቅጽ የያዘ ነው ተብሏል፡፡ 

በሌላ መረጃ “የጫሙትሽካ” የተሰኘ ልብ ወለድ መጽሐፍ ከረዥም ዓመታት በኋላ መልሶ ለንባብ በቃ፡፡ በጉራጌኛ ቋንቋ የተጻፈ የመጀመሪያ ልብ ወለድ ድርሰት የሆነውና በደራሲ ገብረየሱስ ኃይለማርያም የተጻፈው ይህ መጽሐፍ ባሳለፍነው ሳምንት ለሁለተኛ ጊዜ ታትሞ ለንባብ በቅቷል፡፡ ለዓመታት ከገበያ ጠፍቶ የነበረው ይህ ልብ ወለድ መጽሐፍ በዋናነት በፍቅር ላይ ያተኩራል፡፡

ፊልም

“ሶቤክ” የተሰኘ በድርጊት የተሞላ ልብ አንጠልጣይ ፊልም ሊመረቅ ነው፡፡ ተዋናይ ግሩም ኤርምያስ በተወነበትና በጄኢ 123 ስቱዲዮ ተዘጋጅቶ በሜሎክ ኢንተርቴመንት የቀረበው ይህ ፊልም የፊታችን ሰኞሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ነው በብሔራዊ ቴአትር ቤት የሚመረቀው፡፡ በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ ታላላቅ የዘርፉ ባለሙያዎችና በርካታ የጥበብ አፍቃሪያን ይታደማሉ። ከነሐሴ 11 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በተመረጡ ሲኒማ ቤቶች መታየት እንደሚጀምር ታውቋል፡፡

ቴአትር

በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ ከሚታዩ ቴአትሮች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል። የቅርብ ሩቅ ቅዳሜ 8:30 ሰዓት፣ ባሎችና ሚስቶች ደግሞ 11፡30 ሰዓት በብሔራዊ ቴአትር ይታያሉ፡፡ እሁድ ደግሞ በ8፡00 ሰዓት 12ቱ እንግዶች፤  11፡30 ሰዓትእምዬ ብረቷ በዚሁ ቴአትር ቤት ለታዳሚያን ይቀርባሉ፡፡ እንዲሁም በቀጣይ ቀናት ማለት ምማክሰኞ በ11፡30 ሰዓት ሦስቱ አይጦች፣ ረዕቡ በ11፡30 የቅርብ ሩቅ፣ ሐሙስ 11:30 ሸምጋይ፣  አርብ በ11፡30 የሕይወትታሪክ በብሔራዊ ቴአትር ለጥበብ አፍቃሪያን ለዕይታ ይቀርባሉ፡፡

በአብርሃምገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review