በአድዋ ድል መታሰቢያ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የነበረዉ 3ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በ4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ እና ማጠቃለያ ጉባኤ ተጠናቋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በጉባኤዉ ማጠቃለያ የ2018 በጀት አመት የከተማ አስተዳደሩን ቀጣይ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን አመላክተዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች፣ በቀጣዩ በጀት አመት የተጀመረውን ተቋማዊ ሪፎርም አጠናክሮ ማስቀጠል፣ የተቋም አመራሩንና ፈፃሚውን አቅም ለመገንባት በልዩ ትኩረት ይሰራል፤ ሌብነትንና ብልሹ አሰራርን ለማስወገድ የተጀመረው ትግል ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የተጀመረውን የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም በቴክኖሎጂ፣ በአሰራር እና በአደረጃጀት በማስደገፍ ተግባራዊ በማድረግ፣ በፕሮጀክቶች አፈፃጸም ያገኘነውን ድል በአገልግሎት አሰጣጥ እና በመልካም አስተዳደር ለመድገም እንተጋለን ብለዋል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡

መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን በመተግበር እና አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የተጀመረው ጥረት ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል፡፡
የመዲናችንን የገቢ አሰባሰብ በማዘመን የገቢ እቅድን ለማሳካት የተቀናጀ ርብርብ ከማድረግ ባለፈ፣ የከተማችን ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል የቤት ልማት ፕሮግራሞችን በግሉ ዘርፉ፣ በህብረት ስራ ማህበራት፣ በመንግስትና በግል የአጋርነት ፕሮግራም በስፋት ተግባራዊ እናደርጋለን ብለዋል።
በሃገሪቱ ዘላቂ ሰላም እና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የከተማዋን ነዋሪዎች በማሳተፍ በትጋት እንደሚሰራና በመዲናዋ የውሃ አቅርቦትና ሌሎች የተጀመሩ ሜጋ ኘሮጀክቶችን በተሟላ ሁኔታ ለማጠናቀቅ በትኩረት እንደሚሰራም ከንቲባዋ አመላክተዋል፡፡
የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የሌማት ትሩፋትና የከተማ ግብርና ስራዎችን የማስፋቱ ሂደት ተጠናክሮ እንዲሚቀጥል የጠቆሙት ከንቲባዋ፣ በመዲናዋ ጽዳትና ውበት መስክ የተገኘውን ስኬት ከምንጊዜውም በበለጠ እንሰራለን ብለዋል።
የትምህርት ሪፎርም በማጠናከር የትምህርትን ጥራት የማረጋገጥ፣ የጤና አገልግሎቱን ይበልጥ የማሻሻልና የማዘመን እንዲሁም የከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን በማስተዋወቅ እና እንዲጎበኙ በማድረግ ከዘርፉ ከተማዋ ማግኘት የሚገባትን ሁለንተናዊ ፋይዳ እንድታገኝ ለማድረግ እንደሚሰራም አንስተዋል፡፡
የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ፣ አምራች ኢንዱስትሪን የማስፋትና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ ፣ የሰው ተኮር ስራዎችን እንዲሁም የህብረተሰብ ተሳትፎና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎች በይበልጥ ተጠናክረው ይሰራሉ ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ነፃ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ መንግስታዊ የማስተባበርና ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ሚናችንን እንወጣለን ብለዋል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡