12 ቀናትን የፈጀው የዓለማችን ረጅሙ የትራፊክ መጨናነቅ

You are currently viewing 12 ቀናትን የፈጀው የዓለማችን ረጅሙ የትራፊክ መጨናነቅ

AMN- ሐምሌ 06/2017

በርካቶች ምግብና ውሃ እስኪቸገሩ ድረስ በቻይና ብሔራዊ የፍጥነት መንገድ ላይ ተከስቶ የነበረው የትራፊክ መጨናነቅ እጅግ ከባዱ እንደሆነ ይገለፃል፡፡

ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ እርዝማኔ ያለው ሲሆን፣ ለተከታታይ 12 ቀናት የዘለቀ ነበር፡፡

በርግጥ እንደ ሁኔታው ስለሚለያይ ረጅሙን የትራፊክ መጨናነቅ መለየት አስቸጋሪ እንደሆነ ይገለፃል፡፡

በተሸከርካሪ ብዛት ሲታይ በ1990 በጀርመን የተፈጠረው የትራፊክ መጨናነቅ ችግር ቀዳሚው ሲሆን፣ በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይም ሰፍሮ ይገኛል፡፡

በተያዘው የፈረንጆቹ 2025 የካቲት ወር ደግሞ በህንድ ኡታር ፕራዴሽ ውስጥ የተከሰተ ለ48 ሰዓታት የዘለቀውና በርካታ ወረዳዎችን የተሻገረ፣ 300 ኪሎ ሜትር ያህል እርዝማኔ ያለው የትራፊክ መጨናነቅም ተጠቃሽ ነው፡፡

ይሁንና ከጊዜ አንፃር በቻይና ብሔራዊው የፍጥነት መንገድ 110 በተሰኘው ላይ የተፈጠረው ከበድ ያለው ነው፡፡

ነሐሴ 2010 በቻይና ብሄራዊ የፍጥነት መንገድ ላይ በተከሰተው የትራፊክ መጨናነቅ ወቅት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አሽከርካሪዎች በእጅጉ የተቸገሩበት ነበር፡፡

ለ2 ሳምንታት ያለ ምግብ እና ውሃ የታገቱ ያህል መፈናፈኛ አጥተው ሰንብተዋል፡፡

ከሞንጎሊያ ወደ ቤጂንግ የድንጋይ ከሰል እና የግንባታ ቁሳቁሶችን የጫኑ መኪናዎች ለጥገና በከፊል ተዘግቶ የነበረውን አውራ ጎዳና በመዝጋታቸው ምክንያት የተፈጠረ መጨናነቅ ነው፡፡

በአውራ ጎዳናው ላይ ያሉ የአካባቢው ነዋሪዎች የተፈጠረውን ሁኔታ ተጠቅመው ምግብ እና ውሃ በፍጥነት አቅርበዋል፡፡

አንድ ጠርሙስ ውሃ በአንድ ዩዋን ይሸጥ ነበር፡፡

ነገር ግን የትራፊክ መጨናነቁን ተከትሎ አንድ ጠርሙስ ውሃ በ15 ዩዋን በዚያው መንገድ ላይ ተሸጧል፡፡

በሀገሪቱ ታሪክ እጅግ የከፋ የተባለለትን የትራፊክ መጨናነቅ ችግር ለመቅረፍ የቻይና ባለሥጣናት ጥረት ቢያደርጉም ችግሩ ለ12 ተከታታይ ቀናት መዝለቅ ችሏል፡፡

በአውራ ጎዳናው ላይ የተፈጠረው የዓለማችን አሰልቺው እና ረጅም ጊዜ የፈጀ የትራፊክ መጨናነቅ በሚል እውቅና ባይሰጠውም በርካታ የዘርፉ ሰዎች ግን ከዚያ የከፋ የትራፊከ መጨናነቅ አለመኖሩን ያነሳሉ ሲል ኦዲቲ ሴትንትራል አስነብቧል፡፡

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review