የሀገር ውስጥ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትን በጥራትም በስፋትም ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
የኮምቦልቻ ተርሚናል በተያዘው በሐምሌ ወር መጨረሻ እንደሚመረቅ ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ በኢትዮጵያ ትልቁን የአየር ትራንስፖርት የሚሰጠው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይ በ22 ከተሞች የበረራ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም በአፍሪካ ትልቅ አገልግሎት መሆኑን ጠቁመዋል።
አገልግሎቱ አሁንም በቂ አለመሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ደረጃውን በጥራትም ሆነ በስፋት ለማሳደግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከእነዚህም መካከል መንገደኞች የሚስተናገዱባቸው ተርሚናሎች ደረጃቸውን የጠበቁ በማድረግ ረገድ በበርካታ ኤርፖርቶች ከፍተኛ ስራ መሰራቱን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የአዳዲስ የተርሚናሎች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው የኮምቦልቻ ተርሚናል ግንባታ ስራም በተያዘው የሐምሌ ወር መጨረሻ እንደሚመረቅ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በሽሬ፣ ነቀምት እና ደምቢዶሎ አዳዲስ ተርሚናሎች ለመገንባት እቅድ መያዙን ጠቁመዋል።
ነባር የአውሮፕላን መንደርደሪያዎችን በማደስ ትልልቅ አውሮፕላኖችን ማስተናገድ በሚችሉበት ደረጃ ከፍ የማድረግ ስራዎችም እየተሰሩ መሆኑን አመላክተዋል።
ምንም ኤርፖርቶች ባልነበሩባቸው አካባቢዎችም ስድስት ኤርፖርቶች እየተገነቡ መሆናቸውንም ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚው የገለጹት።
ከእነዚህም መካከል የያቤሎ ኤርፖርት በነሐሴ ወር እንደሚመረቅ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
አየር መንገዱ የሀገር ውስጥ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትን በጥራትም ሆነ በስፋት ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።