በመዲናዋ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እምቅ ችሎታችንን እንድናወጣ አግዘውናን ሲሉ ታዳጊዎች ገለፁ

You are currently viewing በመዲናዋ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እምቅ ችሎታችንን እንድናወጣ አግዘውናን ሲሉ ታዳጊዎች ገለፁ

AMN – ሐምሌ 07/2017 ዓ.ም

የከተማ አስተዳደሩ የገነባቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ያለንን እምቅ ችሎታ እንድናወጣ ከማስቻላቸውም ባሻገር፣ ከአልባሌ ስፍራዎችም እንድንርቅ ፋይዳቸው ከፍተኛ ነው ሲሉ ታዳጊዎች ገለፁ፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያት ደረጃውን የጠበቀ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ባለመኖሩ በበጋ የአቧራው ብናኝ፣ እንዲሁም በአባጣና ጎርባጣ ቦታ ላይ የሚገኙት ድንጋዮች አካላዊ ጉዳት ሲያስከትሉባቸው መቆየታቸውን ያስረዳሉ፡፡

ታዳጊዎቹ አክለውም፣ በበጋ ብቻም ሳይሆን በክረምት ጭቃ መሆኑና ስፍራው በሳር መሸፈኑ ለመጫወት ፈታኝ እንደ ነበር ይጠቅሳሉ።

ዛሬ ላይ ሜዳው ጥራቱን ጠብቆ መሠራቱ በጣም ያስደሰታቸው ታዳጊዎቹ፣ በክረምት የእረፍት ጊዜያችን በታዳጊ ቡድን ታቅፈን በቂ ልምምድ በማድረግ እምቅ ችሎታችንን እንድናወጣ አግዞናል ይላሉ።

በስነ ልቦናና በአካል ተነቃቅተን ቀጣዩን የትምህርት ዘመን በጥሩ መንፈስ ከመቀበል ባሻገር፣ የእረፍት ጊዜያችንንም ከአልባሌ ስፍራ እንድንርቅ ረድቶናልም ይላሉ።

አሰልጣኞቹ በበኩላቸው፣ ከተማ አስተዳደሩ ጥራትና ዘመናዊነትን የተላበሱ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን እውን ማድረጉ፣ የታዳጊዎችን የእግር ኳስ ፍላጎት የጨመረ ነው ብለዋል።

የእግር ኳስ ፍላጎት ያለው ታዳጊ በተመቻቸ ሜዳ ተገቢውን ስልጠና ካገኘ ብቃቱን በማሳደግ ተተኪ ስፖርተኛ የማይሆንበት ምንም ምክንያት የለም ያሉት አሰልጣኞቹ፣ በአካል፣ በስነ ልቦናና በእዕምሮ የዳበረ ትውልድ ለመፍጠር ከተማ አስተዳደሩ ለሠራው ስራ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።

በሚካኤል ህሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review