ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ምላሽ ለመስጠት በተግባር የተደገፈ ስራን እያከናወነች እንደምትገኝ ተገለጸ

You are currently viewing ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ምላሽ ለመስጠት በተግባር የተደገፈ ስራን እያከናወነች እንደምትገኝ ተገለጸ

AMN – ሐምሌ 08/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የምታስተናግደውን 2ኛውን የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤን አስመልክቶ ከዓለም አቀፍ ፋውንዴሽኖች፣ ከለጋሽ ተቋማትና ከሲቪክ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ውይይት እየተደረገ ይገኛል።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስዩም መኮንን ኢትዮጵያ የዓለም ስጋት ለሆነው የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ምላሽ ለመስጠት በተግባር የተደገፈ ስራን እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል።

ከዚህም ውስጥ የአረንጓዴ አሻራና የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቮችን ጨምሮ በትራንስፖርት ዘርፉ የሚከሰት የአየር ብክለትን ለመካለከል በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር እንዲገቡ በፖሊሲ ጭምር የተደገፈ ስራን እየሰራች ነው ብለዋል።

ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት በምታከናውነው ተግባራትም በዓለም አቀፍ ተቋማትና ሀገራት በተለይም በፋይናንስ ልትደገፍ ይገባል ብለዋል።

የመድረኩ ዓላማ ሀብት ማሰባሰብና የተለያዩ ግብአቶችን የሚሰበሰቡበትን መደላድል መፍጠር መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ የሚካሔደው 2ኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤም ከኢትዮጵያ ባሻገር በአፍሪካ ደረጃ የሚሰሩ የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከል ስራዎች ለዓለም የሚተዋወቅበት ይሆናልም ብለዋል።

2ኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ “የአረንጓዴ ጉዳይ ውይይቶች አረንጓዴን ማዕከል ያደረጉ እርምጃዎች” በሚል መሪ ሀሳብ ከጷጉሜ 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

በሔኖክ ዘነበ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review