የአዲስ አበባ ቲያትር ቤቶች አስተዳደር ድርጅት አመራሮችና ሰራተኞች በጉለሌ ክፍለ ከተማ በወረዳ 6 ቁስቋም ማሪያም አካባቢ በሚገኘው የወንዝ ዳርቻ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሂደዋል፡፡
የኪነ ጥበብ ባለሙያዎቹ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፣ ኪነ ጥበብና ተፈጥሮ ጥብቅ መስተጋብር ያላቸው በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሊደረግላቸው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ ተሳታፊ የነበሩት አርቲስ ፋንቱ ማንዱየ፣ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የዓለም ሀገራት ድርቅና የጎርፍ አደጋ ከፍተኛ ስጋት እየሆኑ ስለመጡ፣ ይህ ችግር በእኛም ሀገር እንዳይከሰት ሀገራችን የጀመረችውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አጠናክረን ማስቀጠል አለብን ብለዋል፡፡
አርቲስቱ አክለውም፣ በዚህ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የችግኝ ተከላ ላይ በመሳተፋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ ዛሬ እኛ የምንተክላቸው ችግኞች ለነገው ትወልድ የህይወት መሰረቶች ናቸው ብለዋል፡፡

አርቲስት ወለለ አሰፋ በበኩላቸው፣ ዛሬ የምንተክላቸው ችግኞች ለነገው ትውልድ የተሻለችና የአየር ንብረቷ የተጠበቀች ሀገር ለማውረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡
ኪነ ጥበብ ለማንኛውም ሀገርን ለሚጠቅም ነገር ሁሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የገለጹት ደግሞ አርቲስ አሰፋ በየነ ሲሆኑ፣ በዚህ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በመሳተፌ ደስተኛ ነኝ ብለዋል፡፡
አርቲስቱ አክለውም፣ ሁላችንም በዚህ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በመሳተፍ የተሻለ የአየር ንብረት ያላት ሀገር እንድትኖረን እናድርግ ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ቲያትር ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፍጹም ዘገየ በበኩላቸው፣ ኪነ ጥበብና ተፈጥሮ የማይነጣጠልና የተሰናሰለ መስተጋብር እንዳላቸው አመላክተዋል፡፡
የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የሚከውኗቸውን የኪነ ጥበብ ስራዎች ለማሰብና ለማሰላሰል በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከተፈጥሮ ጋር ምናባዊ ተግባቦት እንደሚፈጥሩ ነው ዋና ስራ አስፈፃሚው የገለጹት፡፡
በአስማረ መኮንን