የዱባይ የ20 ደቂቃ ከተማ ራዕይ

You are currently viewing የዱባይ የ20 ደቂቃ ከተማ ራዕይ

AMN- ሐምሌ 8/2017 ዓ.ም

በሰማይ ጠቀስ ህንፃዎቿ የምትታወቀው ከተማ አሁን ደግሞ በምድር ሰፊ ስራዎችን እየሰራች ነው።

የእለት ተዕለት ኑሮን እንደገና በማሰብና ለተሽከርካሪዎች ብቻም ሳይሆን ለሰዎችም ምቹ የሆኑ አካባቢዎችን መፍጠርን ራዕይ ያደረገ ግዙፍ ፕሮጀክት ላይ እየሰራች ነው – ዱባይ።

ይህ የዱባይ የ20 ደቂቃ ከተማ ራዕይ እውን እየሆነ ነው ሲልም ባለቤትነቱ የተባበሩት አረብ ኤምሬት የሆነው ዘ ናሽናል በፊት ገፁ ይዞ ወጥቷል።

ይህ ሃሳብ የሜትሮ ትራንስፖርትን ማስፋፋትና የእግር ጉዞን፣ የብስክሌት እንቅስቃሴን እንዲሁም አረንጓዴ ስፍራዎችን በማበረታታት ላይ አተኩሮ እየተሰራበት ያለ ነው።

የዱባይ የ20 ደቂቃ ከተማ ሃሳብ ነዋሪዎች እንደ መስሪያ ቤት፣ ትምህርት ቤት፣ የግብይት ቦታዎች፣ የጤና ተቋማት እና ሁሉንም አስፈላጊ አገልግሎቶች ከመኪና ነፃ በሆነ መንገድ በእግር፣ በብስክሌት ወይም የከተማ ባቡሮችን ተጠቅመው ከመኖሪያቸው የ20 ደቂቃ ጉዞን ብቻ በማድረግ እንዲያገኙ ማስቻልን አላማ አድርጎ የተነሳ ነው።

የዚህ ሃሳብ አንዱ አካል የሆነው የዱባይ ሜትሮ ሰማያዊ መስመር፣ 5 ቢሊየን ዶላር የተበጀተለት ሜጋ ፕሮጀክት ነው።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በከተማው 14 ጣቢያዎች ያሉት 30 ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍነው የባቡር መስመር በፈረንጆቹ እስከ 2029 ድረስ ይጠናቀቃል ተብሎ እቅድ ተይዞለታል።

አዲሱ የሜትሮ መስመር 20 በመቶ የትራፊክ መጨናነቅን እና የበካይ ጋዝ ልቀትን እንደሚቀንስ እና ፈጣን የትራንስፖርት አማራጭ እንደሚሆን ታምኖበታል።

በተጨማሪም ለኤሌክትሪክ መኪናዎች እና የህዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ገመድ አልባ ቻርጅ ማድረጊያ ቴክኖሎጂዎችንም እየሞከረች ነው።

ከዱባይ የ2040 የከተማ ማስተር ፕላን ውስጥ ተካቶ እየተሰራ የሚገኘው የዱባይ 20 ደቂቃ ከተማ ፕሮጀክት 3 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ አዳዲስ የእግረኛ መንገዶችንም ያካተተ ነው።

ምንም እንኳን በርካታ ነዋሪዎች በእግር እና በብስክሌት የመንቀሳቀስ ፍላጎት ቢኖራቸውም የዱባይ ከፍተኛ ሙቀት ለዛ ምቹ እንዳልሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ይሁንና የመንገድ ላይ ሼዶችን እና የተለያዩ ከፍተኛ የህዝብ ፍሰት እና የአየር ሁኔታን ያማከሉ ንድፎችን እና ዘዴዎችን በመጠቀም የታቀደውን ማሳካት እንደሚቻል ይመክራሉ።

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ዱባይ ሃሳቧን ከማሳካትም ባለፈ ዘመናዊ የሚባሉት ሜትሮፖሊታን ከተሞች እንኳን ለእግረኞች የሚመቹ የሰዎች ከተማ መሆን እንደሚችሉ ተጨማሪ ማሳያ እንደምትሆን ታምኖበታል።

በሊያት ካሳሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review