ለተገልጋዮች በአንድ ቦታ የተለያዩ አገልግሎቶችን ማግኘት የሚያስችለው የሬጅስተራል የአንድ መስኮት አገልግሎት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት መሰጠት ተጀምሯል።
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረትና የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሌሊሴ ደሳለኝ የአንድ መስኮት አገልግሎቱን አስጀምረዋል።

የችሎት ፀሐፊ፣ የሬጅስትራል፣ የፋይል ከፋች፣ የዳታ፣ የመረጃ ዴስክ፣ የፋይናንስ ጉዳዮች እና የመልዕክት ክፍልን ጨምሮ በፍርድ ቤቱ የሚሰጡ አገልግሎቶች በአንድ መስኮት ለማግኘት ያስችላል።
የአንድ መስኮት አገልግሎት መጀመሩ በህገ-መንግሥቱ እና በሌሎች ህጎች መሰረት ነፃና ገለልተኛ በሆነ መንገድ አገልግሎቱን ለተገልጋዮች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችል የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሌሊሴ ደሳለኝ ተናግረዋል።

የአንድ መስኮት አገልግሎቱ፣ በአንድ ቦታ የተለያዩ አገልግሎቶችን ከማስገኘቱ በተጨማሪ ፈጣንና ከዚህ በፊት በተገልጋዮች ይቀርቡ የነበሩ ቅሬታዎችን የሚቀርፍ መሆኑንም ወ/ሮ ሌሊሴ አመላክተዋል።
በሔለን ተስፋዬ