ሩሲያ ለድርድር በሯ ክፍት እንደሆነ እና ለትራምፕ ማስጠንቀቂያም ምላሽ እንደምትሰጥ አስታወቀች

You are currently viewing ሩሲያ ለድርድር በሯ ክፍት እንደሆነ እና ለትራምፕ ማስጠንቀቂያም ምላሽ እንደምትሰጥ አስታወቀች

AMN- ሐምሌ 9/2017 ዓ/ም

ሩሲያ ከዩክሬን ጋር አዲስ ድርድር ለማድረግ ዝግጁ እንደነበረች በመጠቆም፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በዩክሬን ያለው ጦርነት እንዲቆም አሊያም አዲስ ማዕቀብ መጋፈጥ በሚል ለሰጡት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ግን ምላሽ ለመስጠት ጊዜ እንደሚያስፈልጋት ገልፃለች፡፡

በትናንትናው ዕለት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሩሲያ በዩክሬን ላለው ጦርነት እልባት እንድታበጅ 50 ቀናት መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ከሰሜን አትላንቲክ ድርጅት (ኔቶ) አባል ሀገራት ጋር በትብብር ለኬየቭ አዲስ ወታደራዊ ዕርዳታዎችን ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፣ የፕሬዚዳንት ትራምፕ መግለጫ ከበድ ያለ መሆኑን አስታውቀዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ ሞስኮ ምንም አይነት ስምምነት ላይ መድረስ ካልቻለች፣ በሩሲያ የንግድ አጋሮች ላይ ከባድ ቀረጥ እንደሚጥሉ እና ሩሲያ ጦርነቱን መደገፍ የምትችልበትን አቅም እንደሚያሳጧት አስጠንቅቀዋል።

ወደ አራተኛ ዓመት የተሸገረውን ግጭት ለመፍታት የታቀደው የሰላም ድርድር አሁን ላይ መቋረጡ ተነግሯል።

እንደ ቃለ አቀባዩ ከሆነ ሩሲያ አሁንም ለመደራደር ዝግጁ መሆኗን እና በሦስተኛው ዙር ቀጥተኛ የሩሲያ-ዩክሬን ድርድር ላይ ከዩክሬን በኩል ሀሳቦችን እየጠበቀች መሆኑን ገልጸዋል።

በቱርኪዬ በኩል ለሁለት ዙር የተደረገው የሰላም ድርድር ግጭቱን ለማስቆም የሚያስችል ውጤት ማምጣት አለመቻሉ ተዘግቧል።

የትራምፕ ንግግርም ኪየቭን ሊያበረታታ እና የሰላም ጥረቶችን ሊያደናቅፍ እንደሚችል ቃል አቃባዩ ጠቁመዋል።

በብርሀኑ ወርቅነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review