በኢትዮጵያ የሚቲዮሮሎጂ አገልግሎትን ለማዘመን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የአለምአቀፉ የሚቲዮሮሎጂ ድርጅት ዋና ጸሃፊ ሰለስቴ ሳዉሎ (ፕ/ር) ገለጹ፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ከአለምአቀፉ የሚቲዮሮሎጂ ድርጅት ዋና ጸሃፊ ሰለስቴ ሳዉሎ (ፕ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት አስፈጻሚዉ አቶ ጌትነት ጌቱ ሚኒስትሩና ዋና ጸሃፊ ሰለስቴ ሳዉሎ (ፕ/ር) በሚቲዮሮሎጂ አገልግሎት፤ በታዳሽ ኢነርጂ እና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዙሪያ መምከራቸዉን ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) በኢትዮጵያ የሚቲዮሮሎጂ አገልግሎት ለግብርና፣ የጤና የውሃ ሀብት አስተዳደርና ሌሎች ዘርፎችን በብቃት እየደገፈ መሆኑን በዉይይቱ አንስተዋል፡፡

የአየር ጸባይ ትንበያ ስራው አስተማማኝነትና ትክክለኛነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንም ጨምረዉ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ባለፉት አመታት ከ40 ቢሊየን በላይ ችግኞች በመትከል የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስለማድረጉ በዉይይቱ አንስተዋል፡፡
ንጹህ ታዳሽ ኢነርጂ ለቀጠናው ሀገራት በማቅርብም በቀጠናው የካርቦን ልቀት መጠን ቅነሳ ላይ አስተዋጽኦ እያበረከትን ነው ብለዋል፡፡
የአለምአቀፉ የሚቲዮሮሎጂ ድርጅት ዋና ጸሃፊ ሰለስቴ ሳዉሎ (ፕ/ር) በበኩላቸዉ በኢትዮጵያ የሚቲዮሮሎጂ አገልግሎት ያለበት ደረጃ የሚደነቅ መሆኑን አንስተው፤ የአለም ሜቲዮሮሎጂ የአፍሪካ አህጉር ጽ/ቤት በኢትዮጵያ መገኘቱ በአመራር በኩል ያለውን ጥንካሬ ያሳያል ብለዋል፡፡
ዋና ጸሃፊዋ የሚቲዮሮሎጂ አገልግሎትን ለማዘመን አለምአቀፉ የሚቲዮሮሎጂ ድርጅት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናረግዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ