የሚከራዩ አያቶች በጃፓን

You are currently viewing የሚከራዩ አያቶች በጃፓን

AMN – ሐምሌ 09/2017 ዓ.ም

ብቸኝነትዎን የሚያስረሳዎት፣ አጠገብዎ ሆኖ የሚያረጋጋዎት፣ በልምድ ላይ የተመሰረተ ምክር፣ ባስ ሲልም በእርሶ ምትክ ይቅርታ የሚጠይቅሎት ሰው ያስፈልግዎታል? በጃፓን ለዚህ መፍትሄ አለ።

በጃፓን የሚገኘው ድርጅት የተለመደውን የምግብ ማብሰል፣ ፅዳት፣ ልጅ መንከባከብ የመሳሰሉት አገለግሎቶችን ጨምሮ ሌሎችም ያልተለመዱ አገልግሎቶችን ይሰጣል።

ከነዚህ አገልግሎቶቹ ትኩረትን የሳበው ከ60 እስከ 94 ዓመት እድሜ ባላቸው እናቶች የሚሰጠው አገልግሎት ነው።

‘እሺ አያቴ’ የሚል ስያሜን የተሰጠው አገልግሎቱ እነዚህን የእድሜ ባለፀጋ ሴቶች በሰዓት 23 ዶላር በመከራየት ከተለመዱት የቤት አያያዝ አገልግሎቶች በተጨማሪ የስሜት ድጋፍ፣ ልምድ ላይ የተመሰረተ የትዳር ምክርን ማግኘት፤ እንዲሁም በደንበኛው ምትክ ሰርግን ጨምሮ ሁነቶች ላይ የመገኘት፣ ባስ ሲልም የፍቺ እና የስራ መልቀቅ የመሳሰሉ ጉዳዮችን የማሳወቅ፣ ይቅርታን የመጠየቅ አገልግሎቶችን ማግኘት ያስችላል።

በድርጅቱ እ.ኤ.አ በ2012 በተጀመረው የ “እሺ አያቴ’’ ክፍል ብቻ ከ100 በላይ ባለሞያዎች ያሉ ሲሆን በአገልግሎቱ ለማህበረሰብ የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሆነ ታምኖበታል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።

ከዚህ ቀደም በሰዓት 10 ዶላር የሚከራዩ የቪዲዮ ጌም አጫዋቾች፣ ለግብይት፣ ለህክምና ወይም በሌሎች ጊዜያት አብረው የሚሆኑ ወጣቶችን መኖራቸውን ያስታወሰው ዘገባው በጃፓን ሰዎችን የመከራየት አገልግሎቶች እየተለመዱ መምጣታቸውን ዘግቧል።

በሊያት ካሳሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review