የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም የምግብ ዋስትናንም ሆነ የምግብ ሉዓላዊነት ለማሻሻል አግዟል ተባለ

You are currently viewing የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም የምግብ ዋስትናንም ሆነ የምግብ ሉዓላዊነት ለማሻሻል አግዟል ተባለ

AMN- ሐምሌ 9/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በተያዘው የሐምሌ ወር መጨረሻ 2ኛውን ዓለም አቀፍ የምግብ ስርዓት እና ኒውትሪሽን ጉባኤን እንደምታስተናግድ በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽ ኢንስቲቱዩት የኢትዮጵያ ስርዓተ ምግብ ሽግግር እና ኒውትሪሽን ክላስተር አምስት አስተባባሪ አቶ ያለው ማዘንጊያ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት ችግርን ሊያሻግር የሚችል ፍኖተ ካርታ እና ችግሩንም ሊያሻሽሉ የሚችሉ 24 ውጤት ቀያሪ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ቀርፃ እየተገበረች እንደምትገኝ አስተባባሪው ጠቁመዋል፡፡

ይህ እውን እንዲሆንም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ የአስራ ስድስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ኃላፊዎች እና የክልል ፕሬዚዳንቶችን ያካተተ ካውንስል መቋቋሙንም አቶ ያለው ተናግረዋል፡፡

የምግብ ስርዓቱንና የተረፈ ምርቱን አያያዝ የሚከታተሉ ከእርሻ እስከ ጉርሻ በሚል ሰባት ክላስተሮች መቋቋማቸውንና በውስጣቸውም በርካታ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ የልማት አጋሮችን፣ የምርምርና የትምህርት ተቋማትን በአባልነት አካቶ ወደ ተግባር በመገባቱ ጥሩ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑንም አቶ ያለው ገልጸዋል፡፡

እነዚህ አደረጃጀቶች ከሌሎች ሀገራት በተለይም ከአፍሪካ ሀገራት በልዩነት እንድትገኝ እና ሐምሌ 20 ቀን 2017 ዓ.ም የሚጀመረውንና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚመራውን ዓለም አቀፍ የምግብ ስርዓት እና ኒውትሪሽን ጉባኤን ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ ለመመረጥ እንዳስቻሏት አስተባባሪው አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ እየተገበረችው በምትገኘው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም፣ የምግብ ዋስትናንም ሆነ የምግብ ሉዓላዊነት ከማሻሻል አንፃር በርካታ ውጤቶች እንደተገኙበት አቶ ያለው አብራርተዋል፡፡

የበጋ የስንዴ ምርት እድገት መጨመርና ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሰራ ያለው ስራ ለዚህ አንዱ ማሳያ መሆኑንም ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

የጉባኤው ዋነኛ አጀንዳ ከዚህ በፊት በተካሄዱ ጉባኤዎች ላይ ሀገራት የምግብ ስርዓቱን ለማሻገር የገቡትን ቃል በምን ደረጃ እንደተገበሩት የሚገመገምበት፣ ክፍተቶችን እና ጥንካሬዎች የሚለዩበት እንዲሁም የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት ሊሆን እንደሚችልም አመላክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም የሰራቻቸው ስራዎችና ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች ለሌሎች ሀገራት ማሳያ ሆኖ ሊቀርብ እንደሚችል ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review