እንደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት አካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ሪፖርት ከ309 ሚሊየን በላይ ሰዎች በረሃብ በሚኖሩባት ምድር፣ ከ930 ሚሊየን ቶን በላይ ምግብ በዓመት ይባክናል፡፡
ይህ መጠን በ2019 ከነበረበት 1.3 ቢሊየን ቶን ቅናሽ ቢያሳይም፣ ብክነቱ አሁንም በከፍተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
መኖርያ ቤቶች 61 በመቶ የብክነት ድርሻ ሲኖራቸው፣ የምግብ መሸጫዎች ደግሞ 26 በመቶ ድርሻ እንደሚይዙ እና አጠቃላይ በየዓመቱም አንድ ትሪሊየን ዶላር ዋጋ ያለው ምግብ ሳይበላ እንደሚጣል መረጃው ያመላክታል፡፡
ከበለፀጉ ሀገራት እስከ ታዳጊ ሀገራት ችግሩ እንደሚስተዋልም፣ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ለኤኤም ኤን የሰጡ ነዋሪዎች ይገልፃሉ፡፡
የተለያዩ ድግሶችን መሰረት አድርገው በሆቴሎችና በመኖሪያ ቤቶች በሚኖር የቡፌ መስተንግዶ ላይ ከአቅም በላይ ምግብ ማንሳት ለብክነቱ ዋነኛ ምክንያት መሆኑንም ያነሳሉ፡፡
ጤናማ የአመጋጋብ ስርአትን ለመከተል የመጀመሪያው ቁልፍ ተግባር የሚስማማንን ምግብ ብቻ በልክ እና በመጠን ማንሳት መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ይህም ተርፎ ወደ ቆሻሻ የሚጣለውን ምግብ እንዲቀንስ ያስችላል ብለዋል፡፡
በሆቴሎችም ሆነ በተለያዩ ቦታዎች የሚዘጋጁ ድግሶችን መጥኖ ማዘጋጀት እና ተረፈ ምግብን ወደ አማራጭነት መቀየር ብክነትን ለመከላከል ሁነኛ መፍትሄ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
በቢሊየን የሚቆጠር ህዝብ ያላቸው ቻይና እና ህንድ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ምግብ አባካኞች ሲሆኑ፣ በከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጫና እና የኑሮ ውድነት ውስጥ የምትገኘው ናይጄሪያም ሶስተኛዋ ሀገር መሆኗ ተመላክቷል፡፡
ታንዛንያ፣ ዩጋንዳ፣ ሲሺየልስ እና ሩዋንዳ ከፍተኛ የምግብ ብክነት ከሚታይባቸው የአፍሪካ ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
በሚካኤል ህሩይ