AMN ሐምሌ 10/2017
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት የአንድ መስኮት አገልግሎት በማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይ እንደተናገሩት፣ የዳኝነት አገልግሎት ሂደቶች እና ውሳኔዎች የፍርድ ቤቶችን ታማኝነት ከፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
አገልግሎቱ የፍርድ ቤቶች ፍትህን የሚያረጋግጡበትና የስራቸው መለኪያ ሆኖ እንደሚያገለግል አስረድተዋል፡፡
በከፍተኛ ፍርድ ቤት ተግባራዊ የተደረገው የአንድ መስኮት አገልግሎት ፍርድ ቤቶችን ገፅታ በዜጎች አዕምሮቸው ውስጥ እዲቀር የሚያደርግ መሆኑን ኘሬዝዳንቱ ገልፀዋል።
ከዚህ በፊት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተደረገው ጥረት በቦሌና በቃሊት ተመሳሳይ ስራዎች መሰራቱን ጠቅሰዋል፡፡
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ኘሬዝዳንት ወ/ሮ ሌሊሴ ደሳለኝ በበኩላቸው ስራ ላይ የዋለዉ የሬጅስትራር የአንደ መስኮት አገልግሎት የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ፤ ነፃና ገለልተኛ ከማድረግ አንጻር ጉልህ ድርሻ እንዳለዉ ተናግረዋል፡፡
ፍርድ ቤቶች የቀረቡላቸዉን ጉዳዮች በንቃት ከማስተዳደር፤ ህጎችን ዉጤታማ ከማድረግ እና ጉዳዮች በተያዘላቸዉ ጊዜ ዕልባት እንዲያገኙ ከማድረግ አንጻር አገልግሎት የተሻለ አስተዋጽኦ እንዳለዉም ፕሬዝዳንቷ አክለዋል ።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛና የኮርት ማናጀር አቶ አንቢኮ ጃርሳ በበኩላቸው የአንድ መስኮት አገልግሎቱ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን በተቀናጀ መንገድ ለመስጠት የሚያግዝ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ባለጉዳዮች በተለያዪ ቦታዎች የሚደርስባቸውን ውጣውረድ እንደሚቀንስላቸው ገልፀዋል።
ስራ ላይ የዋለዉ የሬጅስትራር የአንደ መስኮት አገልግሎት ተገልጋዮች የተለያዩ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ ለማግኘት እንደሚያስችላቸውም አመላክተዋል፡፡
በሔለን ተስፋዬ