የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለሚያስከብረው መከላከያ ሰራዊት ደም በመለገስ አጋርነታችንን በማሳየታችን ኩራት ይሰማናል ሲሉ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ገለጹ።
የመከላከያ፣ የፍትህ፣ የሰላም ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት አመራርና ሠራተኞች በመከላከያ ሚኒስቴር ጠቅላይ መምሪያ ዋና ግቢ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል የሆነ የደም ልገሳ መርሃ ግብር አካሂደዋል።
የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎቹ ከደም ልገሳው በተጨማሪ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም አከናውነዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርኃ ግብሩ የተዘጋጀው ለመከላከያ ሰራዊት ያለንን አጋርነት ለመግለጽ ነው ብለዋል።
መከላከያ ሰራዊት የሀገሪቱን ዳር ድንበር ከማስከበር ባሻገር ሰላሟን ለማፅናት እያደረገ ላለው ተጋድሎና መስዋዕትነት ደም በመለገስ አጋርነት ለማሳየት የተከናወነ መርሃ ግብር መሆኑንም ገልጸዋል።

ደም መለገስ መልካም ተግባር መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፤ ደም መለገስ የሚችል ሁሉ በዚህ መልካም ተግባር ላይ መሳተፍ እንደሚገባው ተናግረዋል።
የፍትህ ሚኒስትር ሃና አርዓያሥላሴ በበኩላቸው የደም ልገሳ መርሃ ግብሩ የሀገር ዳር ድንበር ለሚያስከብረው መከላከያ ሰራዊት አጋርነት ለማሳየት የተካሄደ ነው ብለዋል።
በዚህ መልካም ተግባር ሁሉም ህብረተሰብ ደም በመለገስ መሳተፍ እንዳለበትም ተናግረዋል።
የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ፤ ትልቁን የህይወት መስዋዕትነት ለሚከፍለው መከላከያ ሰራዊት ደም በመለገሴ ኩራት ይሰማኛል ነው ያሉት።
የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ እንደገለጹት፤ ለሀገር ዳር ድንበር፣ ደህንነትና ሰላም መረጋገጥ ዋጋ እየከፈለ ላለው ሰራዊት ደም መለገስ ተገቢ ነው።
የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ደም ልገሳው ለመከላከያ ሰራዊት ያለኝን አጋርነት ለመግለፅ ነው ሲሉ መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለሚያስከብረው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ደም በመለገሴ ኩራት ይሰማኛል ያሉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን ቢራቱ ናቸው።
ከደም ልገሳው በመቀጠል አመራር አባላቱ በመከላከያ ሚኒስቴር ጠቅላይ መምሪያ ዋና ግቢ አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል።