የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባው፣ የገቢ ግብር ማሻሻያ አዋጅን አፅድቋል፡፡
የገቢ ግብር አዋጁ በስራ ላይ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ በመሆኑ የንግዱን ውስብስብ ባህሪ ያማከለ ዘመናዊ የታክስ አሰባሰብ ስርዓት መዘርጋት አስፋላጊ ሆኖ መገኘቱን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ አብራርተዋል።
ማሻሻያው ከዲጂታል ኢኮኖሚው ጋር የተጣጣመ ዘመናዊ የታክስ መሰረት እንዲኖር ለማድረግና ለታክስ ማጭበርበር በር የሚከፍቱ አሰራሮችን ለመቀየር የሚያስችሉ ድንጋጌዎች መካተታቸውን ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡
የታክስ መሰረትን በማስፋት፣ የመንግስት ገቢ አሰባሰብን በማሻሻል እና የታክስ ፍትሐዊነትን በማረጋገጥ የመንግስትን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የሚያስችሉ ድንጋጌዎች በአዋጁ መካተታቸውን አቶ ደሰላኝ ጠቅሰዋል።

ማሻሻያው ምቹና ቀላል የታክስ ስርዓትን በመዘርጋት ለሀገራችን የተሻለ ኢኮኖሚ ለመፍጠር የሚያስችል እንደሆነም ሰብሳቢው ጨምረው አስረድተዋል፡፡
የገቢ ግብር አዋጅ ማሻሻያ፣ ከግብር ነጻ የሆነው ከመቀጠር የሚገኝ ገቢ ከፍ እንዲል የተደረገ በመሆኑ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ተቀጣሪዎች ላይ የግብር ጫናው እንደሚቀንስ፣ የግብር መሰረቱ እንዲሰፋ፣ መንግስት ከገቢ ግብር የሚያገኘው ገቢ በአንጻራዊ ሁኔታ ከፍ እንዲል አጋዥ መሆኑም በአዋጁ መመላከቱን ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ማሻሻያው ለረጅም ጊዜ ውይይት እንደተደረገበት እና የሀገራት ልምድ እንደተወሰደ ጠቅሰው፣ ማሻሻያው ዘመኑን የዋጀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የመንግስት ሠራተኛውን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል፣ ከገቢ ግብር ማሻሻያ በተጨማሪ የመኖሪያ ቤት ጥናት እየተደረገ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡
ምክር ቤቱም የገቢ ግብር ማሻሻያ አዋጅን በአምስት ተቃውሞ፣ በአሥራ ሁለት ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አፅድቆታል፡፡
በዳንኤል መላኩ