ልክ እንደ ትምህርት ቤት አስተሳሰብና ስብዕናን በመቅረፅ በሀገር ግንባታ ሂደት ትልቅ ሚና ያለው ሚዲያ፣ በአግባቡ ካልተያዘ አፍራሽ ሊሆን እንደሚችል የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮዎች ያሳያሉ፡፡
መገናኛ ብዙሃን ግባቸው የነቃ ማህበረሰብ እና የበለፀገ ሀገርን መፍጠር እንደ መሆኑ መጠን፣ በዚህ ሂደት የሚያጋጥሙ የሌብነት፣ ብልሹ አሰራር እና ሙስናን በመከላከል ረገድ ላቅ ያለ ሚና ሊኖራቸው እንደሚገባ ለኤ ኤም ኤን ሀሳባቸውን የሰጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ማስተማር፣ ማዝናናት እና መረጃ መስጠት የመገናኛ ብዙሃን ተቀዳሚ ተግባር መሆኑን የሚገልፁት የአሃዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጥበቡ በለጠ ናቸው፡፡

ይሁንና በእለት ተዕለት ተግባራቸው ምን ያህል ለሀገርና ህዝብ የሚጠቅም ተግባር ከውነናል የሚለውን መመልከት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
የተሻለ ትውልድ ከመቅረፅ አንፃር መገናኛ ብዙሃን ትልቅ ድርሻ ያበረክታሉ ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህርና ተመራማሪው አብዲሳ ዘርዓይ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣የተከበረ እና ትልቅ ማህበረሰብ መገለጫ የሆነው ሥነ ምግባር እና ሰላም የሚገነባበት አንዱ መንገድ በሚዲያ በኩል መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የህትመት ሚዲያ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ፍቃዱ ተሰማ፣ በጎ ስብዕናን ከመገንባት አኳያ ቤተሰብ፣ የሃይማኖት ተቋማት እና ሚዲያው ያላቸው አበርክቶ የማይተካ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ደረሰ ንጋቱ በበኩላቸው፣ እንደ 4ኛ መንግስት የሚቆጠረው ሚዲያው፣ ማንቃት ላይ በመሥራት ህዝብ በራሱ ጉዳይ ትክክለኛ ውሳኔ ላይ አንዲደርስ በማድረግ የሀገር ግንባታን ያግዛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በፍጥነት ያደጉ ሀገራት ታሪክ ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ሙስናን ለመከላከል ያደረጉት ሚና ጎልቶ እንደሚታይም ያነሳሉ፡፡
ሌብነት ወይም ሙስና የጨለማ ተግባር በመሆኑ ሚዲያው በነዚህ ድርጊቶች ላይ ብርሃን በመፈንጠቅ ማጋለጥ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

መገናኛ ብዙሃን በዓመታዊ እና ወርሃዊ ዕቅዳቸው አካተው ብልሹ አሰራርን ማጋለጥ፣ ግንዛቤ መፍጠር እና የተወሰዱ እርምጃዎች ላይ የሚያተኩሩ ሥራዎችን በቋሚነት ሊሠሩበት እንደሚገባ ያነሳው ደግሞ ጋዜጠኛ ፍትህአወቅ የወንድወሰን ነው፡፡
ለምርመራ ዘገባዎች ልዩ ትኩረት ከመስጠትም ባለፈ በሚቀርቡ ልዩ ልዩ መሰናዶዎች ላይ ሙስናን መከላከል መሰረት ያደረጉ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ቢሠራ በጊዜ ሂደት ሙስናን መቀነስና መከላከል እንደሚቻል የዘርፉ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
በማሬ ቃጦ