ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና የማዕድን ዘርፉን ለማሳደግ ያለመ የኢንቨስትመንት ፎረም በለንደን ማካሄዷን በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኢምባሲ አስታወቀ፡፡
በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኢምባሲ፣ ከኬ ኢ ኤፍ አይ ጎልድ እና ኮፐር ኃ/የተ/የግ/ማህበር እና በአዲስ አበባ የእንግሊዝ ኤምባሲ በጥምረት ባዘጋጁት በዚህ ፎረም ላይ ከ50 በላይ ባለሀብቶች፣ የፋይናንስ ባለሙያዎች፣ የሚዲያ ተወካዮች እና ሌሎች ተሳታፊዎችም መገኘታቸውም ተመላክቷል፡፡
ፎረሙን በንግግር የከፈቱት በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብሩክ መኮንን እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ወደ ግሉ ዘርፍ ኢኮኖሚ የምታደርገው ሽግግር ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ መሻሻሎችና ውጤቶች እየተመዘገቡበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አምባሰደሩ አክለውም፣ ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከ3.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከወርቅ ኤክስፖርት ገቢ ማስመዝገቧ ለዘርፉ እድገት ማሳያ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር አማካሪ ወ/ሮ ሃና ብርሃኑ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ያላትን የበለፀገ የጂኦሎጂ አቅም እና በዘርፉ የተደረጉ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን እንዲሁም ለውጭ ባለሃብቶች የተደረጉ ማበረታቻዎችን ለተሳታፊዎች አብራራታቸዉን ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡