መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ ወደ ዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልፅግና የምታደርገውን ጉዞ ለማፋጠን ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) ገለጹ

You are currently viewing መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ ወደ ዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልፅግና የምታደርገውን ጉዞ ለማፋጠን ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) ገለጹ

AMN ሐምሌ 10/2017

መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ ወደ ዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልፅግና የምታደርገውን ጉዞ ለማፋጠን በጥናት ላይ የተመሰረተና የተደራጀ መረጃን ተደራሽ በማድረግ ሚናቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) ገለፁ።

የለውጡ መንግሥት በወሰዳቸው እርምጃዎች አካታችና ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር ስር እየሰደደ፥ ሀገራዊ ኢኮኖሚውም በከፍተኛ ሁኔታ እያንሰራራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) ለኢዜአ አመራሮች እና ሠራተኞች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች እንዲሁም በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሚኒስትሩ እንዳሉት ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ መንግሥት በወሰዳቸው እርምጃዎች በኢትዮጵያ ምህዳሩ እየሰፋ እና እየተረጋጋ የመጣ አካታች የፖለቲካ ስርዓት እየተገነባ ነው።

የሀገርን ህልውና የሚፈታተኑ የፍትሐዊነትና የእኩልነት አለመኖር ስብራቶችን በመጠገን፥ ለዘላቂ ሰላምና ሀገራዊ አንድነት አስተማማኝ መሰረት መጣሉን አንስተዋል።

በተቃውሞ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በሰላማዊ መንገድ በመንግስት መዋቅር ገብተው እንዲሰሩ መደረጉ፣ በሀገራዊ ምክክር ችግሮችን ለመፍታት ወደ ሥራ መገባቱና የሽግግር ፍትሕ ለዘላቂ ሀገር ግንባታ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ስርዓታዊ ልህቀት ማምጣት የሚያስችሉ ነፃና ገለልተኛ የዴሞክራሲ እና የጸጥታ ተቋማት መገንባታቸውንም ነው ሚኒስትሩ ያነሱት።

የለውጡ መንግሥት በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይልና በአመራር ጠንካራ የጸጥታና ደህንነት ተቋማት መገንባቱ፥ ከየትኛውም አቅጣጫ በኢትዮጵያ ላይ ሊቃጣ የሚችልን ጥቃት በሩቁ የሚያስቀር አስተማማኝ አቅም እንዲፈጠር አስችሏል ብለዋል።

በሀገረ መንግስቱ ላይ አደጋ ደቅነው የነበሩ ቡድኖች መንግሥት በፈጠረው አቅም፣ ዓለም አቀፍ ሁኔታው በመቀየሩና በራሳቸው የተሳሳተ አካሄድ ከነበሩበት እብሪት ወርደው ህልውናቸው ወደማክተም እየሄደ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያን የጸጥታ ኃይሎች የሚገዳደር ኃይል የለም ነው ያሉት።

መንግሥት ለሀሳብ የበላይነት ዋጋ በመስጠቱ፣ የወል ትርክትን እየገነባ በመሆኑ፣ የኢኮኖሚ ሪፎርምን በመተግበሩ፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን እየፈታ በመሆኑና ህግን በማስከበሩ ተጨባጭ ድሎች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ሌብነትና ብልሹ አሰራርን የማይሸከም ስርዓት በመገንባት የመንግስት አገልግሎትን የማዘመን ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በችግር ውስጥ ሆና በልማት ስራዎች ስኬት ማስመዝገቧን ገልጸው፥ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችና በብዝሃ ዘርፍ ልማት ሀገራዊ ኢኮኖሚው በአካታችነት እያንሰራራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

መንግሥት በቀጣይ ኢ-ተገማችና ቅፅበታዊ ዓለም አቀፍ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረገና ችግሮችን በመቅረፍ ድሎችን ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ሀገርን ከማንሰራራት ወደ ተሟላ ብልጽግና ለማሸጋገርም በተለወጠ ሀገራዊ ዕይታ ለአዳዲስ እመርታዎች መዘጋጀቱን ማረጋገጣቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

መገናኛ ብዙሃንም አካታች የፖለቲካ ስርዓቱ ይበልጥ እንዲጎለብት፣ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ እንዲጠናከር በጥናትና በተደራጀ መረጃ ተደራሽነት አጋዥ ሚናቸውን ማጎልበት አለባቸው ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review