በቦሌ ክፍለ ከተማ በመንግሥት እና በማህበረሰብ ተሳትፎ የተገነቡ ማስፋፊያ የተደረገላቸው ትምህርት ቤቶች ተመርቀዋል።
በምረቃ መርሀግብር ላይ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ጀማሉ ጀምበር (ዶ/ር )ትምህርት ቤት ትውልድ የሚቅረጽበት እና ሀገርን የሚገነባበት ማዕከል በመሆኑ የትምህርት ቤት ግንባታና ማስፋፊያ ላይ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራን ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቶቹ መጪው ትውልድ በአካል ፣ በስነልቦና ፣ በእውቀት እና በክህሎት ብቁ እንዲሆኑ የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ለትምህርት ዘርፉ በተሰጠው ትኩረት ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረው፣ ለአብነትም ትምህርት በፈረቃ ይሰጡ የነበሩ ትምህርት ቤቶች መቀነስ መቻሉንና ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹ እንዲሆኑ መደረጉን አንስተዋል፡፡
የቦሌ ክፍለ ዋና ስራ አስፈፃሚ እሸቱ ለማ (ዶ/ር) የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ እና ማስፋፊያ ጥራት ያለው ትምህርት ለትውልድ ለመስጠት እና የተማሪ የክፍል ጥምርታ ደረጃን የሚያስጠብቅ ነው ብለዋል።
ከለውጡ ወዲህ የህዝብን ጥያቄ የሚመልሱ በርካታ ፕሮጀክቶች መሰራታቸውን ጠቅሰው ለትምህርት ዘርፉ በተሰጠው ትኩረትም መሻሻሎች መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡
በዳንኤል መላኩ