ጉባኤውን አስመልክቶ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሳዓዳ አብዱረህማን መግለጫ የሰጡ ሲሆን፣ ጨፌው 6ኛው ጨፌ ኦሮሚያ 4ኛ ዓመት 9ኛ መደበኛ ጉባኤው የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ምክክር በማድረግ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ገልጸዋል።
በዚሁ መሰረት የ2017 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርትን እንደሚያዳምጥ እና የ2018 በጀት ዓመት እቅድን እንደሚመለከትም አፈ ጉባኤዋ ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ የልማት፣ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በጥልቀት ይታያሉም ተብሏል።
ጨፌው በጉባኤው የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2017 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም እንደሚገመግም እና አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥም ተመላክቷል።
በተለይም የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍትህን ከማስፈን እና በቴክኖሎጂ በመደገፍ ስራዎችን ከማከናወን አኳያ የተከናወኑ ስራዎች እንደሚታዩም አፈ ጉባኤዋ አብራርተዋል።
ጨፌው የኦዲት ዋና መስሪያ ቤት አፈጻጸምን እንደሚመለከት እና ረቂቅ አዋጆች እና ሹመቶች እንደሚኖሩ ተገልጿል።
ጉባኤው ሐምሌ 12 እና 13 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተመላክቷል፡፡
በሀብታሙ ሙለታ