በዚህ የክረምት በጎ ፈቃድ የ90 ቀናት ንቅናቄ 60 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ከአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ጋር በመተባበር ዛሬ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተደረገ የደም ልገሳ መርሀግብር ከ1 ሺህ 1 መቶ በላይ የደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች ደም እንዲለግሱ ተደርጓል፡፡
በከተማ ደረጃ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለያዩ ሁነቶች እንደቀጠለ ይገኛል፡፡
በሻምበል አበበ ቢቂላ ስታዲየም የአዲስ አበባ በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ከደንብ ማስከበር ባለስልጣን ጋር በመተባበር ከ1 ሺህ 1 መቶ በላይ የደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች የመርሃ ግብሩ አካል የሆነ የደም ልገሳ አካሂደዋል።
በዚህም ከ11ዱም ክፍለ ከተሞች ከእያንዳንዱ 100 የደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች እንዲሳተፉ መደረጉ ነው የተመላከተው፡፡
በዚህ የክረምት የ90 ቀን በጎ ፈቃድ ንቅናቄም ከ60 ሺህ ዩኒት በላይ ደም ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝና እስካሁንም ድረስ ከ20 ሺህ ዩኒት በላይ ደም እንደተሰበሰበ የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ይመር ከበደ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ዋና ስራአስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ አባላቱ የማህበረሰቡን ሰላምና ጸጥታ እንዲሁም ህግ ከማስከበር በተጨማሪ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ በፈቃደኝነት ደም ልገሳ እና ሌሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ በነቂስ እየተሳተፉ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ተመሳሳይ የደም ልገሳዎችም ቢያንስ በየሶስት ወሩ በማካሄድ የማህበረሰቡ አለኝታ መሆናቸዉንም ለማሳየት በትጋት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
በየሺዋስ ዋለ