የባህል ቡድኑ ወደተለያዩ የአለም ሀገራት የሚያደርገው ጉዞ የኢትዮጵያን ህያው ባህል በማስተዋወቅ አዲስ ምእራፍ የሚከፍት መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለጹ

You are currently viewing የባህል ቡድኑ ወደተለያዩ የአለም ሀገራት የሚያደርገው ጉዞ የኢትዮጵያን ህያው ባህል በማስተዋወቅ አዲስ ምእራፍ የሚከፍት መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለጹ

AMN ሃምሌ 11/2017 ዓ.ም

“ኪን ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ብስራት” የተሰኘ የኢትዮጵያን ባህል ለአለም የሚያስተዋውቅ የባህል ቡድን ወደ ተለያዩ የአለም ሀገራት ጉዞ እንደሚያደርግ ተገልጿል ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ እና የሻኩራ ፕሮዳክሽን ስራ አስኪያጅ አርቲስት ካሙዙ ካሳ ሁነቱን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሀን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ሁነቱ የኢትዮጵያን ህያው ባህል ለአለም ህዝብ በማስተዋወቅ አዲስ ምእራፍ የሚከፍት መሆኑን ገልጸዋል።

ኪነጥበብ የአንድን ሀገር እሴት በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸው፤ ሁነቱ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው የኢትዮጵያን የባህል ዲፕሎማሲ ከፍ የሚያደርግ መሆኑንም ጠቁመዋል።

መንግስት ኪነጥበብ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ ሰፋፊ ስራ መስራቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ገጽታ በመገንባት እንዲሁም ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም አመላክተዋል።

የጉዞው የመጀመሪያ መዳረሻ ቻይና መሆኑን ገልጸው በቀጣይ ወደ ተለያዩ ሀገራት ጉዞውን እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በርካታ የኪነጥበብ ሀብት ያላት ሀገር ናት ብለዋል።

ሁነቱ የኢትዮጵያን ባህል በአለም አቀፍ ደረጃ በጉልህ የሚያስተዋውቅ መሆኑን በመግለጽ።

በሁነቱ የባህል ትርኢት፣ የእደ ጥበብ ውጤቶች፣ ትርኢት እንዲሁም ከሀገራት ጋር የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት መሆኑን መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ላለፉት አራት ወራት የተለያዩ ዝግጅቶች ሲደረጉ መቆየቱን የገለጹት ደግሞ የሻኩራ ፕሮዳክሽን ስራ አስኪያጅ አርቲስት ካሙዙ ካሳ ናቸው።

በሁነቱ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ባህል፣ አመጋገብና ባህላዊ አለባበሶች እንደሚቀርቡበት ተናግረዋል።

የባህል ቡድኑ እሁድ ሀምሌ 13 ጉዞውን ወደ ቻይና በማድረግ እንደሚጀምር ተጠቁሟል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review