የአረንጓዴ ሽፋኑ መጨመር አንድምታ

You are currently viewing የአረንጓዴ ሽፋኑ መጨመር አንድምታ

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር የኢትዮጵያ ህዝብ በስፋት እየተሳተፈባቸው ከሚገኙ ስራዎች መካከል በቀዳሚነት ይቀመጣል። በመርሀ ግብሩ የዕድሜ፣ የፆታ፣ የሃይማኖትና ሌሎች ልዩነቶች ሳይስተዋሉ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በአንድነት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

ወይዘሮ ሪታ ፈቃዱ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 በተለምዶ ድል በር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ የአረንጓዴ ዐሻራ ከተጀመረ አንስቶ ባለፉት ዓመታት በተከታታይ ችግኝ በመትከል ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ዛፍ የሰው ልጅ ለመኖር እጅግ አስፈላጊ የሆነው ኦክሲጂን ምንጭ ነው። እያጋጠመ ያለውን ከፍተኛ ሙቀት፣ ድርቅ፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብና የጎርፍ አደጋዎችን ለመቆጣጠር ያስችላል፡፡ ከምንም በላይ ጥቅሙ “ለራሴ፣ ለከተማዬና ለሀገሬ ነው” በሚል መነሻ ችግኝ በመትከል እየተሳተፉ እንደሆነ ወ/ሮ ሪታ ይናገራሉ፡፡

ባለፉት ዓመታት ከመቀጠያ እስከ እንጦጦ ማርያም ባለው አካባቢ ችግኞችን ተክለዋል፡፡ በመኖሪያ ቤት ቅጥር ግቢያቸው ውስጥ ባላቸው አነስተኛ ቦታም ባለፈው ዓመት ፅድ እና ለምግብነት የሚውሉ እንደ ኦቦካዶና አፕል ያሉ የፍራፍሬ ችግኞችን ተክለዋል። እነዚህ ችግኞች ሲወጡ እና ሲገቡ ሲመለከቷቸው ለዓይናቸው ተስፋና ደስታን እየፈጠረላቸው ይገኛል። ችግኞቹ ሲያድጉም እንደ ጥላ በመሆን ከፀሐይ ሀሩር መከላከያ እንዲሁም ለምግብነት እንደሚውሉም ተናግረዋል፡፡

ዘንድሮም ወይዘሮ ሪታ ወደ እንጦጦ መውጫ አርሴማ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የሚገኝ ስፍራ ላይ አሻራቸውን አኑረዋል።፡ በችግኝ ተከላ ላይ ሲሳተፉም ከፍተኛ ደስታና እርካታ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ “ችግኝ ስተክል ውስጤን በጣም ደስ ይለዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ለከተማና ለሀገር ጥቅም ከፍተኛ ትርጉም ያለውን አሻራ በማሳረፍ የራሴን ድርሻ እየተወጣሁ እንደሆነ ይሰማኛል” ይላሉ፡፡

ችግኝ ከመትከል ባሻገር የተተከሉት እንዲፀድቁ በሚሰሩበት የጉለሌ ክፍለ ከተማ የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ጽህፈት ቤት በኩል በየጊዜው ውሃ በማጠጣት ክትትል እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል፡፡ 

አቶ አዳሙ ዘገየ ሌላኛው በአረንጓዴ ዐሻራ ንቁ ተሳትፎ ከሚያደርጉት መካከል ናቸው፡፡ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 በተለምዶ ጨረታ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ አዳሙ፣ ከዚህ ቀደም የምኖርበት አካባቢ በደን የተሸፈነ፣ ንፁህ ወንዞችና ጅረቶች ኩልል እያሉ የሚፈሱበት ነበር፡፡ ከነዋሪው ቁጥር መጨመርና አዳዲስ ሰፈሮች መመስረት ጋር ተያይዞ የደንና አረንጓዴ ሽፋኑ እየተመናመነ ሲመጣ ይህንን ለማስተካከል የበኩሌን ድርሻ ለመወጣት ችግኝ ወደ መትከልና መንከባከብ ገባሁ ይላሉ፡፡

አቶ አዳሙ በሚኖሩበት ወረዳ የአረንጓዴ ልማት አምባሳደር ናቸው። እስከአሁንም በጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል፣ እንጦጦ ጫካና በአካባቢያቸው በተለያዩ ስፍራዎች ጉድጓድ በመቆፈርና ችግኝ በመትከል ተሳትፈዋል፡፡ በሰፈር የተለያዩ ዕድሮች አመራር እንደመሆናቸው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ማህበረሰቡ ችግኝ እንዲተክልና እንዲንከባከብ ግንዛቤ በመፍጠርና በማስተባበር እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

“ችግኝ መትከልና መንከባከብ ያስደስተኛል፡፡ ችግኝ የህልውና መሰረት ነው፡፡ ምግብ፣ ልብስ፣ ጥላ እና ውበት ነው፡፡” የሚሉት አቶ አዳሙ እሳቸውን ጨምሮ ማህበረሰቡ በሚያደርገው ተሳትፎ በሰፈራቸው ንፁህና አረንጓዴ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ነው፡፡ ለአብነትም በወረዳ 5 ክልል ውስጥ የሚገኘው አወሊያ የሙስሊም ትምህርት ቤት እና በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ስር በሚገኘው ቅዱስ ፍራንቺስኮ ገዳም አካባቢ የቆሻሻ መጣያ የነበሩ ስፋራዎች፣ በአግባቡ ታጥረው ችግኝ ተተክሎባቸው ውብ፣ ጽዱና አረንጓዴ ሆነዋል፡፡ በዘንድሮው ዓመት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብርም በግላቸው እስከ 200 ችግኞች ለመትከል ማቀዳቸውን ነግረውናል።

አዲስ አበባ እና አረንጓዴ ዐሻራ

በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከል፣ የምግብ ዋስትናን እና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጥ የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በ2011 ዓ.ም ተጀምሮ ባለፉት ስድስት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ተተክሏል፡፡

በአዲስ አበባም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ከተጀመረበት አንስቶ ባለፉት ዓመታት በየዓመቱ በከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ በሚሊዮን የሚቆጠር ችግኝ እየተተከለ ነው፡፡ በ2011 ዓ.ም 6 ሚሊዮን፣ በ2012 ዓ.ም ከ8 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ፣ በ2013 ዓ.ም ከ11 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ፣ በ2014 ዓ.ም ከ14 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ፣ በ2015 ዓ.ም ከ17 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ እንዲሁም በ2016 ዓ.ም ከ27 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ተተክሏል፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት በድምሩ 85 ሚሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል፡፡ በአዲስ አበባ በ2017 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ከ4 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ችግኝ ለመትከል ዕቅድ ተይዟል፡፡

በአዲስ አበባ ደረጃ የ2017 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብርን ባስጀመሩበት ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደገለፁት፣ ባለፉት ስድስት ዓመታት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር አማካኝነት የከተማዋ የአረንጓዴ ሽፋን ከ2 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 22 በመቶ ማደግ ችሏል፡፡ ከተተከሉት ውስጥም ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑት ችግኞች ፀድቀዋል፡፡

አረንጓዴ አሻራ  ለመዲናዋ የሚያስገኘው ትሩፋት

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2017 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት፣ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶችን እያመጣ ይገኛል፡፡ አረንጓዴ ዐሻራው ኢኮኖሚውን እያነቃቃ ነው፡፡ ቱሪዝምን ብናነሳ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት አንድም ውብ የሆነውን መልክዓ ምድሯን ለማየት እና ንጹህ፣ ምቹና ተስማሚ በሆነው የአየር ንብረቷ በመማረክ ነው። በኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከልነት ኢትዮጵያ ተመራጭ እንድትሆን አረንጓዴ ዐሻራ የማይተካ ሚና ተጫውቷል፡፡ በተያዘው ዓመትም ከ100 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች ኢትዮጵያ ውስጥ መካሄዳቸውን ለማሳያነት አንስተዋል፡፡

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያም አዲስ አበባ እንደሀገር ከተገኘው ትሩፋት ምን ያህል ተጠቃሚ እየሆነች እንደሆነ ያመለክታል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት፣ በከተማዋ ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ደርቀው የነበሩ ወንዞችና ጅረቶች ፍሰት ጎልብቷል፤ ጠፍተው የነበሩ ምንጮች መፍለቅ ጀምረዋል። በአፈርና ስነ ምህዳር ጥበቃ ትላልቅ ለውጦች መታየት ጀምረዋል፡፡ የተተከሉ ችግኞች ጥላ፣ ውበት፣ የቱሪስት መስህብ፣ ምግብ በመሆን እንዲሁም የስራ ዕድልና ገቢ በማስገኘት የሚታይና የሚጨበጥ ለውጥ መጥቷል፡፡

የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በሆርቲካልቸር፣ ሁለተኛ ድግሪያቸውን ደግሞ በአካባቢ የአየር ንብረት አስተዳደር ዘርፍ ያጠኑትና በጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል የሆርቲካልቸር ልማት ዳይሬክተር አቶ መክብብ ማሞም ይህንን ይጋሩታል፡፡

አዲስ አበባ የኢትዮጵያውያን መዲና ብቻ ሳትሆን የአፍሪካና የዓለም የዲፕሎማሲ ከተማ ናት፡፡ ችግኝ በመትከል የአረንጓዴ ሽፋኗን ማሳደግ ላይ የተሰሩ ስራዎች ከስም ባሻገር የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን የሚያስመሰክሩ ናቸው፡፡ በችግኝ ተከላው በአረንጓዴ የተሸፈነ ምቹና ሳቢ የስራና የመኖሪያ አካባቢ መፍጠር ተችሏል። ተራራማ አካባቢዎች፣ መሀል ከተማ፣ መዝናኛ ስፍራዎች፣ የመንገድ አካፋዮችና ክፍት ቦታዎች አረንጓዴ በመልበሳቸው ሙቀትን በመቀነስ ሚዛኑን የጠበቀ የአየር ንብረት እንዲኖር አዎንታዊ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ 

ችግኞች በተተከሉ ቁጥር ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን ካርቦንዳይኦክሳይድ ዕፅዋቶች ስለሚጠቀሙት የሙቀት አማቂ ጋዞች ክምችት እንዲቀንስ ያደርጋሉ፡፡ በሀገር ደረጃ ካሉ ተሽከርካሪዎች አብዛኞቹ በአዲስ አበባ የሚገኙ ናቸው፡፡ የዕፅዋት ሽፋን ማደግ ማለት ከተሽከርካሪዎች የሚወጣና ወደከባቢ አየር የሚለቀቅ ጋዝ መቀነስ ማለት እንደሆነ አቶ መክብብ ያስረዳሉ፡፡

የችግኝ ተከላው ከመዝናኛ ፓርኮች ባሻገር ወንዝና የወንዝ ዳርቻዎችን የሚሸፍን በመሆኑ ከዚህ ቀደም ውበት አልባ የነበሩ ወንዞች የህይወት ምንጭ እንዲሆኑ እያደረገ ነው፡፡ ከመነሻቸው ከእንጦጦ ጀምሮ በሚሰራው ስራ ወንዞች እየጠሩ፣ የድሮ ወዝና መልካቸውን እየያዙ መጥተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ሥነ ቀመር ኮሌጅ የአካባቢ ሳይንስ ማዕከል መምህርና ተመራማሪ የሆኑት መኩሪያ አርጋው (ፕሮፌሰር) ከአንድ ወር በፊት ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ 96 ነጥብ 3 ኤፍ ኤም፤ አጀንዳ ፕሮግራም ላይ በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት፣ የአረንጓዴ ዐሻራ በከተማዋ የከርሰ ምድር ውሃ አቅርቦት ዘላቂነት እንዲኖረው ትልቅ ፋይዳ ይጫወታል፡፡ ደኖች ሲመናመኑ በዛፎች አማካኝነት ወደ መሬት የሚሰርገው የውሃ መጠን ይቀንሳል፡፡ ይህም የከርሰ ምድር ውሃ መጠን እንዲቀንስ ያደርጋል። ዛፎች ካልተተከሉ ለበርካታ ዓመታት እንዲያገለግሉ የሚቆፈሩ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች የውሃ አቅርቦት ይቀንሳል። ከዚህ አኳያ በከፍተኛ ቦታዎች የሚተከለው ዛፍ የሚወጣውን ውሃ መልሶ መተካት ያስችላል፡፡  

የችግኝ ተከላው የቆሻሻ መጣያ በሆኑ፣ የተረሱ ስፍራዎች ላይ ጭምር የሚካሄድ በመሆኑ እነዚህ አካባቢዎች ንፁህ፣ አረንጓዴና ውብ ገፅታን ተላብሰው ሰዎች የሚዝናኑባቸውና መንፈሳቸውን የሚያድሱባቸው አካባቢዎች ሆነዋል፡፡ መኩሪያ (ፕ/ር) እንደሚሉት መንግስትና ህዝብን ከፍተኛ ወጪ ከሚጠይቁ ጉዳዮች አንዱ ጤናን ለመጠበቅ የሚወጣው የህክምና ወጪ ነው፡፡ የአረንጓዴ ሽፋን መጨመር፣ ወንዝና የወንዝ ዳርቻዎች ንፁህ መሆን ጤናን ለመጠበቅ በተለይ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

ይህ ብቻ አይደለም አረንጓዴ ስፍራዎች የሰለጠነ፣ ርዕይ ያለው ማህበረሰብ ለመፍጠር ይረዳል፡፡ ሰዎች ቁጭ ሲሉ ነው የሚፈጥሩት፡፡ ሰው ቆሻሻ ቦታ ላይ ተቀምጦ፣ ደስ የማይል ነገር እያየ ጥሩ ነገር ማሰብ አይችልም፡፡ ጥሩ የሚያስብና የተሻለ ለመስራት ዝንባሌ ያለው ማህበረሰብ ለመፍጠር እንደሚያግዝ የአካባቢ ሳይንስ ማዕከል መምህርና ተመራማሪው አብራርተዋል፡፡ 

የአረንጓዴ ዐሻራ ማህበራዊ ጥቅሞችንም እያስገኘ እንደሆነ አቶ መክብብ ይገልፃሉ፡፡ በአንድ በኩል በችግኝ ተከላ ጊዜ በተለያየ የዕድሜ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ አብረው የሚያሳልፉበትና የሚተዋወቁበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ በተጨማሪም መዝናኛ ቦታዎች ውብ፣ አረንጓዴና ሳቢ በመሆናቸው የሰርግ፣ የልደትና የተለያዩ መርሀ ግብሮች ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የሚገናኝበት ሁኔታ በመፍጠር ማህበራዊ ትስስር እንዲጠናከር ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡

አረንጓዴ ዐሻራው በከተማ ደረጃ ውስን የነበሩ ችግኝ ጣቢያዎች፤ አሁን በየክፍለ ከተማው እንዲቋቋሙና በእነዚህ ጣቢያዎች ችግኝ እየፈላ፣ ችግኝ መትከል ባህል እየሆነ እንዲመጣ በር መክፈቱንም አቶ መክብብ ያነሳሉ፡፡

ባለፉት ዓመታት የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ ከተከናወነባቸው አካባቢዎች ጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል አንዱ ነው፡፡ ማዕከሉ 705 ሄክታር ስፋት ያለው ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም አብዛኛው ስፍራ በባህር ዛፍ የተሸፈነ ነበር፡፡ በየዓመቱ ባህር ዛፉን በማንሳት በሀገር በቀል ዕፅዋት በመተካት በሚሰራው ስራ በአካባቢው ጠፍተው የነበሩ ምንጮች ተመልሰዋል። የዕፅዋት ዓይነቶችም ጨምረዋል፡፡ ብርቅዬ የዱር እንስሳትና አዕዋፍትም ወደ ማዕከሉ እንዲገቡ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አቶ መክብብ ያስረዳሉ፡፡

Addis Ababa Climate Action Plan (2021-2025) በሚል ርዕስ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከC40 የከተሞች የአየር ንብረት አመራር ቡድን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሰነድ እንደሚያሳየው በአዲስ አበባ የአረንጓዴ ቦታዎች ሽፋን መመናመን እስከ 40 በመቶ ለሚሆነው የጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋዎች መከሰት አስተዋፅኦ አለው፡፡

ከዚህ አኳያ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የችግኝ ተከላና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የጎርፍ አደጋ ስጋትን በመቀነስ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኝ አቶ መክብብ ያስረዳሉ። ለምሳሌ በጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል በተራራማ ቦታዎች የሚፈጠረውን ጎርፍ ውሃ አቁረው የሚይዙ ጉድጓዶችን በመገንባት፣ የሚተርፈው ውሃ ደግሞ ተፈጥሯዊ ፍሰቱን ጠብቆ እንዲወርድ የጎርፍ መቀልበሻ በመስራት በታችኛው ተፋሰስ አካባቢ ያጋጥም የነበረውን ጎርፍ መከላከል ተችሏል፡፡

የአረንጓዴ ዐሻራው  መርሀ ግብር ለበርካታ ወገኖችም የስራ ዕድል ፈጥሯል። አሁንም የጉለሌ ዕፅዋት ማዕከልን ለማሳያነት ብናነሳ ከዚህ ቀደም በአረንጓዴ ልማት የተሰማሩት ከ200 የማይበልጡ የቀን ሰራተኞች ነበሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ700 በላይ ሰራተኞች በዕፅዋት ልማትና ብዜት፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ እንዲሁም በመዝናኛ ልማት ተሰማርተው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ የአረንጓዴ ዐሻራ ሲጀመር የማዕከሉ የዕፅዋት ብዜት አቅም 100 ሺህ አልደረሰም ነበር። በ2012 ዓ.ም 550 ሺህ፣ 2013 ዓ.ም 560 ሺህ፣ በ2014 ዓ.ም 720 ሺህ እያለ እያደገ መጥቶ አሁን እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርስ ሀገር በቀል የዕፅዋት ችግኝ በማባዛት ማቅረብ ተችሏል፡፡ ችግኝ የሚፈላበት ስፍራ በዓመት ዜሮ ነጥብ ስምንት ሄክታር ከነበረበት ወደ ሶስት ሄክታር ማሳደግ እንደተቻለ አቶ መክብብ አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ለችግኝ ተከላ የሚካሄደው ቅድመ ዝግጅትም ተሻሽሏል፡፡ ችግኝ መትከል ባህል እየሆነ መጥቷል፡፡ ከተከላ በኋላ ያለው እንክብካቤ ላይ መሻሻሎች ቢኖርም አሁንም ክፍተቶች አሉ፡፡ ከዚህ አኳያ “ከተከልን መንከባከብ አለብን” በሚል መርህ መስራት እንደሚገባ አቶ መክብብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የችግኝ ተከላና የአረንጓዴ ሽፋን መጨመር ለአዲስ አበባ ዘርፈ ብዙ ትርጉም ያለው ተግባር ነው፡፡ የከተማዋን እስትንፋስ የማስቀጠል፣ ውበቷንና የዜጎችን ጤና የማስጠበቅ፣ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ ቱሪዝምን የማሳደግ፣ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው፡፡ በጥቅሉ ከተማዋን ለኑሮ ምቹና ተስማሚ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የሚያግዝ ቁልፍ መሳሪያ ነው፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review