ምግባቸውን እያመረቱ ያሉ ከተሞች

You are currently viewing ምግባቸውን እያመረቱ ያሉ ከተሞች

• ለንደን ከመደበኛው ግብርና አንፃር 70 በመቶ የውሃ ፍጆታ የሚቆጥብ የምድር ውስጥ የከተማ ግብርና ታከናውናለች

ከተሞች የኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሞተር ናቸው፡፡ በርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2023 ያወጣው ጥናታዊ ፅሑፍም ይህንኑ ያመላክታል። ተቋሙ ከተሞች በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በከባቢያዊ ስርዓቶቻችን ውስጥ ምን ድርሻ አላቸው? (What are Cities and What Role do They Play in our Social, Economic, and Environmental Systems?) በሚል ርዕስ ያስነበበው ጥናታዊ ፅሑፍ እንደሚያትተው ከሆነ ከተሞች የንግድ፣ የሥራ ዕድል እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ማዕከል በመሆን ለሀገራት ሁለንተናዊ ዕድገት ከፍተኛ ሚና ያበረክታሉ፡፡

በዓለም ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት (ጂ.ዲ.ፒ) ላይም ከተሞች ትልቁን ድርሻ እንደሚያበረክቱ ይኸው ጥናታዊ ፅሑፍ ያመላክታል። በጥናታዊ ፅሑፉ መሠረት ከተሞች በዓለም ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ውስጥ የ85 በመቶ ድርሻ ያበረክታሉ። የተሻለ የመሠረተ ልማት ዝርጋታቸው፣ ግዙፍ ሞሎች፣ መዝናኛ ስፍራዎች፣ የቱሪዝም መስህቦች፣ እንደ ሆቴል፣ ሆስፒታል እና የኮንፈረንስ ማዕከላት ያሉ አገልግሎት አቅራቢዎች ተቋማት ከተሞች ለዓለም ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ የሚያስችሏቸው ሀብቶች ናቸው፡፡

ቱሪዝም መስህቦች፣ እንደ ሆቴል፣ ሆስፒታል እና የኮንፈረንስ ማዕከላት ያሉ አገልግሎት አቅራቢዎች ተቋማት ከተሞች ለዓለም ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ የሚያስችሏቸው ሀብቶች ናቸው፡፡

በአብዛኛው ተዝናኖታዊ ቅኝት ያላቸው የስራ እንቅስቃሴዎች እንደሚዘወተርባቸው የሚገመተው ከተሞች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግብርናንም እንደ አንድ የኢኮኖሚ ምንጭ መጠቀም ጀምረዋል። አይግሮው ኒውስ፣ ‘ምግባቸውን የሚያመርቱ ከተሞች’ በሚል ርዕስ ያዘጋጀው ፅሑፍ፣ የከተማ ግብርና በውስን ቦታ ላይ ትርጉም ባለው ደረጃ የከተማ ነዋሪዎችን አኗኗር እያሻሻለ እንደሚገኝ አስነብቧል፡፡

እንደ ሲንጋፖር፣ ዲትሮይት፣ አትላንታ፣ ሚያሚ፣ ለንደን፣ ኒው ዮርክ እና ፓሪስ ያሉ ከተሞች በአነስተኛ ቦታዎች ላይ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተለያዩ የግብርና ስራዎችን በመስራት ነዋሪዎቻቸውን ተጠቃሚ አድርገዋል፡፡ ለምሳሌ በዶሮ፣ በወተት፣ በዓሣ፣ በአትክልትና በፍራፍሬ ምርቶች እንዲሁም በተፈጥሮ ሀብት ልማት ረገድ ቀላል የማይባል ውጤት አግኝተዋል። ምርቶቹን ለቤት ውስጥ ፍጆታ ከማዋል ባሻገር አቀነባብረው ለሽያጭ በማዋልም ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ፈጥረዋል፡፡

የሲንጋፖር ከተማ 10 በመቶ ያህሉን የምግብ ፍጆታዋን በከተማ ግብርና ለመሸፈን በቅታለች፡፡ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2030 ከሚያስፈልጋት የግብርና ምርት ውስጥ 30 በመቶውን  በራሷ ለመሸፈን በመስራት ላይም ትገኛለች፡፡ ለዚህም ‘30 by 30 Goal’ የተሰኘ መርሃ ግብር ነድፋ እየሰራች ሲሆን፣ በከተማ ግብርና ዙሪያ ፈጠራን ለማበረታታት 60 ቢሊዮን ዶላር መመደቧን ‘World Economice Forum,’ “Urban Farms And Food Security In Singapore” በሚል ርዕስ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2021 ያወጣው ፅሑፍ ያትታል፡፡

ሰማይ ጠቀሶቹ የሲንጋፖር ህንፃዎች በተለያዩ የአትክልት እና ፍራፍሬ ዝርያዎች የተሞሉ ናቸው፡፡ የግድግዳቸው ዙሪያ እንደ ሐረግ በተንዠረገጉ ልዩ ልዩ የአትክልትና ፍራፍሬ እፅዋት የተሸፈኑ ናቸው፡፡ ጣሪያቸውም ‘የግብርና ምርት የሚታፈስባቸው ማሳ’ ከሆኑ ሰነባብተዋል።

ሲንጋፖር በክፍት ቦታዎቿ ብቻ ሳይሆን ከመኪና ማቆሚያነት የተረፉ የህፃዎቿን ምድር ቤቶች ሁሉ ሳይቀር ውሃ ሞልታባቸው የዓሳ ማርቢያ አድርጋቸዋለች። በዚህም በመቶ ሺህ ቶን የሚቆጠር የዓሳ ምርት በየዓመቱ ታገኛለች፡፡

ሲንጋፖር በከተማ ግብርና ዘርፍ መሰማራት ለሚሻ ዜጋዋ የገንዘብ ድጋፍ ታደርጋለች፡፡ አትክልትና ፍራፍሬ የማምረት ፍላጎት ላላቸው ዜጎቿ 83 ሚሊዮን ዶላር መመደቧ በመረጃው ተመላክቷል፡፡

የሚቺጋኗ ዲትሮይት በከተማ ግብርና ስራ ቀዳሚ ስፍራን ከሚይዙ ከተሞች ተርታ ትሰለፋለች፡፡ በቀደሙት ጊዜያት የዲትሮይት ከተማ ነዋሪዎች በሰፋፊው ቅጥር ግቢያቸው የውበት እፅዋትን እና ሳር በመትከል ይታወቃሉ፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በእነዚህ ክፍት ቦታዎች ልዩ ልዩ የአትክልት፣ የፍራፍሬ እና የሰብል አይነቶችን በማምረት የምግብ ፍጃታቸውን ወደ ማሟላት ስለመሸጋገራቸው ‘One Earth’ የተሰኘ ገፀ ድር፣ ‘From urban gardens to agrihoods: The rise of agricultural neighborhoods in Detroit’ በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ በ2025 ለንባብ ያበቃው ፅሑፍ ያትታል፡፡

በዚህ ፅሑፍ መሠረት፣ 1 ሺህ 400 የዲትሮይት ከተማ ነዋሪዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ የከተማ ግብርና ዘርፍን ተቀላቅለዋል፡፡ እነዚህ የከተማዋ ነዋሪዎች በጓሯቸው በቆሎን ጨምሮ ሌሎች ሰብሎችን፣ ጥራጥሬዎችን፣ አትክልቶችን እና ፍራፍሬዎችን ያመርታሉ፡፡ በዚህም የቤት ውስጥ ፍጆታ ከማሟላት አልፈው ምርቶቻቸውን ለሱፐር ማርኬቶች በማስረከብ ተጨማሪ ገቢ ያገኛሉ፡፡

ለንደን በዘመናዊ የከተማ ግብርና ስራ መልካም ስም እና ዝና እየገነባች ስለመምጣቷ Science Direct ገፀ ድር እ.ኤ.አ በ2023 ያስነበበው ፅሑፍ ያትታል። ለንደን ከሌሎች ከተማዎች በተለየ የምድር ውስጥ የግብርና ቴክኖሎጂን ይዛ ብቅ ብላለች፡፡ ይህም ከግንባታዎች በታች የሚገኝን የምድርን ውስጠኛ ክፍል ለግብርና ስራ ማዋል ነው። ይህ ስራ ከፍተኛ ወጪ፣ ቴክኖሎጂና ጊዜ የሚጠይቅ ቢሆንም ውጤቱ ያማረ ስለመሆኑ በፅሑፉ ተመላክቷል፡፡

ለንደን የምድር ውስጥ ግብርና ያካሄደችው ከመደበኛው የግብርና ስራ በተለየ ጥቅሞችን ስላገኘችበት እንደሆነ የሚያትተው ፅሑፉ፣ በ33 ሜትር ጥልቀት የተዘጋጀው ይህ የከተማ ግብርና ማከናወኛ ዋሻ ከመደበኛው የግብርና ስራ በተለየ የውሃ ፍጆታን 70 በመቶ ይቆጥባል፤ ምርታማነቱ ደግሞ በእጥፍ ይበልጣል (በመደበኛው የምድር ላይ ግብርና በአንድ ሄክታር መሬት 20 ኩንታል ምርት የሚገኝ ሲሆን፣ በምድር ውስጥ ግብርና በሄክታር 40 ኩንታል ምርት ይገኛል እንደማለት ነው)፡፡

ይህ ግብርና ያለ አፈር የሚከናወን ሲሆን፣ በአፈር ቦታ ታዳሽ ምንጣፍን ይጠቀማል፡፡ እንደየአትክልት አይነቱ የሚለያይ ቢሆንም በፍጥነት የሚደርሱትን በዓመት አራት ዙር የማምረት ዕድል እንደሚሰጥም ተጠቁሟል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ለከተማ ግብርና ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በ3ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉበዔ ላይ የ2017 ዓ.ም አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፣ የከተማ ግብርናን ከማስፋትና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ከማሳደግ አኳያ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል፡፡

ማህበረሰቡ በከተማ ግብርና ልማት ስራ ላይ ያለው ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች፣ የተሳታፊዎች ቁጥር እና የከተማ ግብርና ምርትም ስለማደጉ መናገራቸው ይታወሳል። በከተማ ግብርና በዚህ ዓመት ብቻ 280 ሺህ 406 ቶን ምርት ማግኘት ተችሏልም ብለዋል፡፡

እንደ ከንቲባ አዳነች ማብራሪያ 2 ሺህ 188 አርሶ አደሮች በግል ይዞታቸው ላይ በከተማ ግብርና ስራ ተሰማርተዋል። አርሶ አደሮች ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገቡ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ረገድም ጥረት ተደርጓል፡፡ እስከ አሁን በከተማ ግብርና ስራ ውስጥ የታቀፉ የከተማዋ ነዋሪዎች ዶሮ፣ እንቁላል፣ ወተት፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ እና ሰብሎችን በማምረት ኑሮአቸውን አሻሽለዋል፡፡

በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2050 የዓለም ህዝብ ቁጥር 10 ነጥብ 2 ቢሊዮን እንደሚደርስና የምግብ ፍላጎቱ አሁን ካለው በ70 በመቶ ከፍ እንደሚል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ትበያ ያመላክታል። ይህም አማራጭ የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ ስልቶች እንደሚያስፈልግ ጠቋሚ ነው፡፡ ታድያ የከተማ ግብርና ስራ ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ እሙን ነው።

የዓለም ህዝብ ቁጥር መጨመር፣ የከተሜነት መስፋፋት፣ የአካባቢና የአየር ንብረት ተፅዕኖዎች እየተባባሱ መምጣት የምግብ ዋስትና ጉዳይ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው ከሚያስገድዱ ምክንያቶች በቀዳሚነት ተጠቅሰዋል፡፡

ችግሩን ለመቋቋም ከተቀመጡ የመፍትሔ አማራጮች መካከል ደግሞ ዘመናዊ የከተማ ግብርናን ማስፋፋት አንዱ ነው። የከተማ ግብርና ምርትና ምርታማነትን በመጠንም በጥራትም በማሳደግ ኢኮኖሚን ይደጉማል፤ በከተማና በከተማ ዙሪያ የሚኖረውን ህብረተሰብ የስርዓተ-ምግብና የምግብ ዋስትና እንዲሻሻልም ጉልህ አበርክቶ እንዳለው ታምኖበት እየተሰራበት ይገኛል፡፡

በተካልኝ አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review