በከተሞች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብ የከተማ ግብርና ዘርፍ አንድ አማራጭ ሆኖ እየተሰራበት ይገኛል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማም በርካታ ነዋሪዎች በዶሮና በወተት ላም እርባታ፣ በከብት ማድለብ፣ በንብ ማነብ፣ በሰብል እና በሌሎችም ዘርፎች ተደራጅተው በመስራት ውጤታማ እየሆኑ መጥተዋል። ነዋሪዎች በመኖሪያ ቤት ቅጥር ግቢ፣ ትምህርት ቤትን ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት የጓሮ አትክልቶችን በመትከል የምግብ ፍጆታቸውን እየሸፈኑ አለፍ ሲልም ገቢ እያገኙና የስራ ዕድል እየፈጠሩ ነው፡፡
በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 በከተማ ግብርና ዘርፍ የተሰማሩት አርሶ አደር ናትናኤል ባጫ ቀድሞ ጤፍ፣ ሽምብራ፣ ጓያ በማምረት ኑሯቸውን ሲመሩ ቆይተዋል። በተጨማሪነት በምን መልክ ቢሰሩ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንዳለባቸው ባለማወቃቸው የሚፈለገውን ምርት ማግኘት እንዳልቻሉ ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡
በወረዳው በከተማ ግብርና ባለሙያዎች ግንዛቤ ከተሰጣቸው በኋላ በስራቸው ውጤታማ መሆን፣ ገቢያቸውም እያደገ መምጣቱን አልሸሸጉም፡፡ ባገኙት ግንዛቤ በጓሮ አትክልት ዘርፍ ከ2013 ዓ.ም አንስቶ የሀበሻ ጎመን፣ ቆስጣ፣ ጥቅል ጎመን፣ ሰላጣ በማምረት ከእለት ጉርስ አልፎ ለገበያ በማቅረብ ገቢ ያገኛሉ፡፡ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ በ8 ሺህ ብር ካፒታል የተጀመረው የጓሮ አትክልት ስራ 900 ሺህ ብር ካፒታል አፍርቶላቸዋል፡፡ ቀድሞ በአንድ ክፍል ቤት ባልተመቻቸ ሁኔታ ይኖሩ የነበረው አሁን አራት ክፍሎች ያለው የተሻለ መኖሪያ ቤት መስራትም ችለዋል፡፡
አርሶ አደሩ የከተማ ግብርና ስራን ከማጠናከር ጎን ለጎን በ2014 ዓ.ም ስንዴን ወደ ማምረት ተሸጋገሩ፡፡ በ1 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ በ25 ሺህ ብር ካፒታል የጀመሩት የስንዴ ማምረት ስራ አሁን ላይ የምርጥ ዘር፣ የማዳበሪያ፣ የአረም ማጥፊያ መድኃኒት መግዢያን ችሎ 70 ሺህ ብር ካፒታል ማፍራት ችለዋል፡፡ በጓሮ አትክልቱ ለ3 ዜጎች ቋሚ እና ለ5 ጊዜያዊ እንዲሁም በስንዴው ስራ ለ3 ዜጎች የሥራ እድል ፈጥረዋል፡፡
“የከተማ ግብርና ባለሙያዎች የስራ ቦታዬ ድረስ በመምጣት ስንዴን በመስመር እንዴት መዝራት እንዳለብኝ በሃሳብም፤ በተግባርም አሳይተውኛል። ማዳበሪያ በወረዳ ደረጃ በተመጣጣኝ ዋጋ ይቀርብልናል፡፡ በዚህም በከተማ ግብርና ዘርፍ በመስራቴ ውጤታማ እየሆንኩ እገኛለሁ፡፡ በቀጣይም ስራዬን አሻሽዬ በመስራት ለሌሎች ዜጎች ተጨማሪ የሥራ እድል የመፍጠር እንዲሁም በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች በዘርፉ ቢሰማሩ ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ የመስራት እቅድ አለኝ” ብለዋል፤ አርሶ አደር ናትናኤል፡፡
ባለሙያዎች ግንዛቤ በመስጠት ረገድ ድጋፍ እንዳደረጉላቸው የሚያስታውሱት አርሶ አደሩ፣ “ማምረት ከጀመርኩ በኋላ ያየኝ ባለሙያ የለም፡፡ ውጤቴን ቢያዩ የበለጠ እበረታታለሁ” ሲሉ የድጋፍ ስራው ቀጣይነት ባለው መልኩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ከአርሶ አደር ቤተሰብ የወጡት ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ሀሰን በሽር በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 በከተማ ግብርና ዘርፍ እየሰሩ ይገኛሉ። ከቤተሰባቸው ባገኙት ልምድ በ2008 ዓ.ም በወተት ላም እርባታ ላይ ተሰማሩ። በአንድ የወተት ላም የተጀመረው ስራ አሁን ላይ 25 የወተት ላሞች ደርሰዋል። በቀን 250 ሊትር ወተት ለሽያጭ ማቅረብ፣ ለ10 ዜጎችም የሥራ እድል መፍጠር ችለዋል፡፡
አቶ ሀሰን የከተማ ግብርና ውጤታማ እያደረጋቸው መሆኑን፣ “ጠንክሬ በመስራቴ ልጆቼን ማስተማርና ቤተሰቤን በተገቢው ማስተዳደር ችያለሁ፡፡ ለመኖሪያ ቤት እና ለስራ የሚሆን አንድ ፒክ አፕ መኪና ሀብት ማፍራት ችያለሁ። 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ካፒታልም አፍርቻለሁ” ሲሉ ገልፀዋል፡፡ የከተማ ግብርና ባለሙያዎች በሚሰሩት ስራ ሙያዊ ድጋፍ እያደረጉላቸው ቢሆንም የመኖ ዋጋ መናር ስራቸውን በአግባቡ ለመስራት እንቅፋት እንደሆነባቸውም አክለዋል፡፡
ኮሚሽኑ በዘርፉ ለተሰማሩት ምን ድጋፍ እያደረገ ነው?
የዝግጅት ክፍላችን በከተማ ግብርና በተለይ በእንስሳት እና ዕፅዋት ዘርፍ ለተሰማሩ አካላት ምን ድጋፍ እያደረገ ነው ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽንን ጠይቋል፡፡ በኮሚሽኑ የእንስሳት እርባታ ባለሙያ አቶ ቢኒያም አድማሱ በሰጡት መረጃ፤ በዋናነት በእንስሳት እርባታ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ዜጎች በአካል በመሄድ የድጋፍና ክትትል እንዲሁም የማማከር ሙያዊ ስራ ይሰራል። በወተት ላም፣ በዶሮ፣ በዓሳ፣ በንብ ማነብ፣ በከብት ማድለብ ላይ እንዴት መስራት እንዳለባቸው፣ በምን ሁኔታ ቢሰሩ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ወረዳ ድረስ በመውረድ ይሰጣቸዋል፤ ለስራቸው አጋዥ የሆነ መረጃ በበራሪ ወረቀት መልክ በማዘጋጀትም እንዲሁ፡፡ የአመጋገብ፣ የውሃ አጠቃቀም፣ ግብአት ላይ እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ስልጠናም ይሰጣል፡፡
ባለሙያው እንዳስረዱት፤ ለአርሶ አደሮች በማዕከል ባሉ ባለሙያዎች ከሚሰጠው የማማከርና ድጋፍ ስራ ባለፈ በወረዳ እና በክፍለ ከተማ ደረጃ ባሉ ባለሙያዎች የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡
በኮሚሽኑ የዕፅዋት ቴክኖሎጂ ግብአት አቅርቦት አመቻች ባለሙያ አቶ ኢሳያስ አበበ በተመሳሳይ እንደገለፁት፤ በከተማ ግብርና ዘርፍ በአብዛኛው በጓሮ አትክልት፣ በሰብልና ሌሎችም ላይ እየሰሩ ለሚገኙ አካላት የተሻለ ውጤት እንዲያገኙ፣ ምርትን ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ አሰራሮችን እንዲከተሉ የሙያ ድጋፍ ይሰጣል፡፡ ይህም ሥነ ምህዳርን መሰረት በማድረግ የትኛው አካባቢ የተሻለ ምርት እንደሚሰጥ፣ በመስመር መዝራት፣ ዘር ሲዘራና ከተዘራ በኋላ በምን መልኩ ክትትል መደረግ እንዳለበት እና ሌሎችም ላይ የማማከር ስራ ይሰራል፡፡ አርሶ አደሮች በተመጣጣኝ ዋጋ ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ እንዲያገኙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የማመቻቸት ስራም በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ከዚህ ባለፈ በከተማ ግብርና የተሰማሩ አርሶ አደሮች ማሳ ላይ መስሪያ ቦታቸው ድረስ በመውረድ የማዳበሪያ አጣጣል፣ የዘር አጠቃቀም፣ የተባይና የበሽታ ቁጥጥር ላይ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ባለሙያው ገልፀዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እና የኤክስቴንሽን ዘርፍ ኃላፊ አቶ መለሰ አንሼቦ እንደገለፁት፤ ከሀገራዊ ለውጡ በፊት የከተማ ግብርና ዘርፍ በንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ስር በዳይሬክቶሬት ደረጃ ሆኖ ሲሰራበት ቆይቷል፡፡ ከለውጡ ወዲህ መንግስት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠቱ በ2011 ዓ.ም “የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን” በሚል ስያሜ ራሱን ችሎ እንዲቋቋም አድርጓል። በዚህም በከተማ ግብርና በዋናነት በእንስሳት ዘርፍ የእንቁላል፣ የዶሮ ስጋ፣ የበሬ፣ የበግና ፍየል ስጋ፣ የማርና የዓሳ ምርቶች ትኩረት ተደርጎ እየተሰራባቸው ነው፡፡ በዕፅዋት ዘርፍ ደግሞ በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ የሚመረቱ የአትክልት እና ፍራፍሬ እንዲሁም የሰብል ምርቶች፣ ከአርሶ አደሩ ማሳ ውጪ ደግሞ በከተማ ውስጥ በሚከናወኑ የአትክልት ምርቶችና በሌሎችም ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡
በዘርፉ ውጤት ለማምጣት የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን አቶ መለሰ ያስረዳሉ፡፡ ለአብነት የግብርና መዋቅሩን ከከተማ እስከ ወረዳ በየደረጃው መዘርጋት፣ በእንስሳት እርባታ፣ በዕፅዋት ልማት፣ በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት ድጋፍና ክትትል ማድረግ፣ በባለሙያዎችም የግብርና ስራ በከተማ ውስጥ እንዴት ማከናወን እንደሚቻልና ፍላጎቱ ያላቸው ወደ ዘርፉ ገብተው እንዲሰሩ የማስተማር፣ የስልጠናና የኤክስቴንሽን አገልግሎት መስጠት ይጠቀሳሉ፡፡
በተጨማሪም በዘርፉ ለሚሰማሩ አካላት ግብአት እንዲያገኙ የማመቻቸት ስራ የሚሰራ ሲሆን ለአብነት በዶሮ እርባታ ለሚሰማሩ የእንቁላል ጣይ ዶሮ እና የዶሮ ጫጩት ከሚያቀርቡ አካላት ጋር በማስተሳሰር ግብአቶቹን ካገኙ በኋላ በምን መልክ ማምረት እንዳለባቸው ስልጠና ይሰጣል፡፡ እንዲሁም የእንስሳት መኖ፣ ማዳበሪያ እንዲቀርብ የማድረግና ሌሎችም የኤክስቴንሽን አገልግሎት በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህ ተግባራት በመከናወናቸው በአሁኑ ወቅት በእንስሳት እና በዕፅዋት ዘርፍ የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች 1 ሚሊዮን 28 ሺህ ደርሰዋል፡፡ ይህ ትልቅ ውጤት ነው ብለዋል፡፡
ምክትል ኮሚሽነሩ እንዳስረዱት፤ ከተማ ለመኖሪያነት፣ ለንግድና ለሌሎች ክዋኔዎች የሚሆን እንጂ ለግብርና ስራ ይሆናል ተብሎ የሚታሰብ አልነበረም። መንግስት በሰጠው ልዩ ትኩረት ይህ አመለካከት ተቀይሮ፤ የከተማ ግብርና ተተግብሮ ውጤት ከማምጣቱ ባሻገር ባህል ሆኖ እየተሰራበት ያለ ዘርፍ ሆኗል። በመሆኑም በአዲስ አበባ ከተማ አሁን ላይ እንቁላል ለቤተሰብ ፍጆታ በግላቸው የሚያመርቱ እና ተደራጅተው ለገበያ የሚያቀርቡ ያሉ ሲሆን በከተማዋ በቀን ከ2 ሚሊዮን በላይ እንቁላል ይመረታል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከፍጆታ አልፎ ከ509 ሺህ በላይ እንቁላል ለገበያ ይቀርባል፡፡ ወተት በቀን ከ100 ሺህ ሊትር በላይ ይመረታል፡፡ ሌሎችም ምርቶች ለገበያ እየቀረቡ በመሆኑ የከተማ ግብርና ለኢኮኖሚው እድገት አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡ በከተማ ግብርና ዘርፉም በ2013 ዓ.ም 109 ሺህ 347፣ በ2014 ዓ.ም 289 ሺህ 763፣ በ2015 ዓ.ም 423 ሺህ 95፤ በ2016 ዓ.ም 721 ሺህ 905 እንዲሁም በ2017 ዓ.ም 1 ሚሊየን 28 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
በእንስሳት ዘርፍ የተሰማሩ አካላት እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን ገልፀው ነገር ግን የእንስሳት መኖ ዋጋ መናር ስራቸውን በሚፈለገው ልክ ለማከናወን ተግዳሮት መፍጠሩን አንስተዋል፡፡ ለዚህ ምን ምላሽ አለዎት? ላልናቸው ጥያቄ ምክትል ኮሚሽነሩ በሰጡት ምላሽ፣ “ትክክል ነው፤ የመኖ ዋጋ መናር መኖሩ ይታወቃል፡፡ የዋጋ መናሩ እየተከሰተ ያለው በሁለት ምክንያቶች ነው፤ ለመኖ ማቀነባበሪያ የሚሆኑ ግብአቶች ዋጋ መጨመር እና ከዚህ በፊት ያልነበረ 15 በመቶ የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) በመኖ ላይ በመጨመሩ ነው፡፡ ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት ሙሌ የመኖ ማቀነባበሪያ የተሰኘ መኖ ባህር ዳር አምርቶ አዲስ አበባ አምጥቶ የሚሸጥ ካምፓኒ በቦሌ ክፍለ ከተማ በመንግስት ቦታ ተሰጥቶት 50 ሺህ ኩንታል መያዝ የሚችል መጋዘን በመገንባት እያመረተ እንዲያቀርብ ውል ተደረገ፡፡ በዚህም መሰረት የደላሎች እጅ ሳይገባበት መኖው በመዲናዋ የሚገኙ አምራቾችና አከፋፋዮች ከሚሸጡበት በዝቅተኛው ዋጋ ምርቱን በ11ዱም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ 25 ሸማች ሱቆች በኩል ለተጠቃሚዎች እንዲቀርብ እየተደረገ ነው። ከፍ ያለ ቁጥር የሚጠቀሙት ደግሞ ከመጋዘኑ እየመጡ እንዲገዙ ይደረጋል፡፡ ይህ ማለት ግን የመኖ ዋጋ ንረትን ፈትተናል ማለት አይደለም፡፡
ከዚህ ባለፈ የውሃ እጥረት እንዳለ በተደጋጋሚ የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡ ችግሩን ለመፍታት ከዚህ ቀደም ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ የውሃ ቦቴዎች በከተማ አስተዳደሩ ስላሉ ቦቴዎቹን ተረክበን በእንስሳትና በእፅዋት ዘርፍ ለተሰማሩ አካላት ውሃ ለማቅረብ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም የከርሰ ምድር ውሃ በማውጣት እንዲጠቀሙ ለማድረግ የማመቻቸት ስራም እየተከናወነ ይገኛል” ብለዋል፡፡
በከተማ ግብርና ዘርፍ በመሰማራት ውጤታማ መሆን እንደሚቻል በባለሙያ ግንዛቤ የተሰጠ ቢሆንም ስራ ከጀመርን በኋላ ያመጣነውን ውጤት በሚፈለገው ሁኔታ ወርደው ማየት ቢችሉ እንበረታታለን በሚል ለተነሳው አስተያየት አቶ መለሰ ሲመልሱ፤ “በወረዳ፤ በክፍለ ከተማና በከተማ ደረጃ ያሉ ባለሙያዎች ወርደው ክትትልና ድጋፍ ያደርጋሉ። ነገር ግን በከተማ ግብርና ዘርፍ የተሰማሩ አካላት ከአንድ ሚሊዮን በላይ በመሆናቸው እያንዳንዳቸው ጋር ለመድረስ የባለሙያ እጥረት አለ፡፡ በወረዳም እጥረቱ ይስተዋላል፡፡ በተጨማሪም ባለሙያዎች በዘርፉ ስራ ላይ ያለመቆየት ችግርም አለ፡፡ በመሆኑም ይህን ችግር ለመቅረፍ መዋቅሩን በማየት ጥናት ተደርጎ ባለሙያዎች እንዲሟሉ በትኩረት ይሰራል” ሲሉ ገልፀዋል፡፡
የከተማ ግብርና ዘርፍን ለማስፋፋት በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት የሚደረጉ ማንኛውም የድጋፍና ክትትል ስራዎችን ማስቀጠል፣ ችግሮቻቸውን በመለየት መፍትሔ የመስጠትና ሌሎችም ስራዎች በትኩረት የሚሰሩ መሆናቸውን የሚገልፁት አቶ መለሰ፣ በግቢው ሰፊም ይሁን ጠባብ ቦታ ያለው ማንኛውም ህብረተሰብ የከተማ ግብርናን ማከናወን ስለሚቻል ጠንክሮ በመስራት ከጓሮው ትኩስና ንፁህ ምርት በማምረት ለእለት ጉርሱ ተጠቃሚ እንዲሆን መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በ2022 ዓ.ም አዲስ አበባ የከተማ ግብርና የተስፋፋባት፤ የአርሶ አደሩ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የተረጋገጠባት እና ከአፍሪካ ከተሞች በዘርፉ ተምሳሌት የሆነች ከተማ የማድረግ ርዕይ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ምክትል ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል፡፡
በሰገነት አስማማው