በመዲናችን አዲስ አበባ ባለፉት ቀናት የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ስራዎች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል። ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም መሰል ዝግጅቶች ይቀርባሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የቴአትር ምርቃት፣ የመጽሐፍት ውይይቶችና የሥዕል አውደ-ርዕይ ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የተወሰኑትን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡
መጽሐፍት
ዛሬ ቅዳሜ ከቀኑ 9:00 ሰዓት ጀምሮ የገጣሚ አንዱ ጌታቸው የግጥም መድብል በሆነው “ስካርፍ፣ ቡና እና ጢስ” በተሰኘው የግጥም መድብል ላይ ውይይት ይደረጋል፡፡ አራት ኪሎ ኢክላስ ሕንጻ ውስጥ በሚገኘው በዋልያ መጽሐፍት አዳራሽ የሚደረገው ይሄ ውይይት፣ የጥበብ አፍቃሪያን ተገኝተው የውይይቱ አካል እንዲሆኑ ተጋብዘዋል።
በሌላ መረጃ፣ “የወዲያ ነሽ” ልብወለድ መጽሐፍ እንደገና ለንባብ ሊበቃ ነው፡፡ በአንጋፋው ደራሲ ሃይለመለኮት መዋዕል የተደረሰው ይህ መጽሐፍ ለዓመታት ከገበያ ጠፍቶ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ እንደገና ለአንባብያን እንዲደርስ እየተሰራ መሆኑ ደራሲው አሳውቋል፡፡
የደራሲው የመጀመሪያ ድርሰት የሆነው ይኸው ልብወለድ መጽሐፍ፣ በቅድመ-ሽያጭ ዘዴ በማህበራዊ ሚዲያ በኩል ለገበያ ቀርቧል፡፡ የመጽሐፉ ዋጋ 400 ብር ሲሆን፣ አንባብያን በደራሲው በኩል መጽሐፉን እንዲገዙና ያሉበት ቦታ ድረስ እንደሚልክላቸው በማህበራዊ የትስስር ገጹ አሳውቋል፡፡
ሥዕል
“የቀለማት ግለ-ዝና” የተሰኘና የሰዓሊ እያሱ ተላይነህ የሥዕል ሥራዎች የቀረቡበት አውደ-ርዕይ ሐምሌ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በሀያት ሪጀንሲ በሚገኘው ፈንድቃ የባህል ማዕከል በመታየት ላይ ነው፡፡ አውደ-ርዕዩ እስከ ፊታችን ሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ለጥበብ አፍቃሪያን ክፍት ሆኖ ይቆያል።
ሲኒማ
በታዋቂዋ የፊልምና የቴአትር ባለሙያ መዓዛ ወርቁ የተጻፈውና የተዘጋጀው “እመጌቶች” ቴአትር ነገ እሁድ ሐምሌ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ከምሽቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ ይመረቃል፡፡ ቴአትሩ የሚመረቀው በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል ውስጥ በሚገኘው ፈንድቃ የባህል ማዕከል ሲሆን የጥበብ ወዳጆች ምርቃቱ ላይ ተገኝተው እንዲመለከቱ ተጋብዘዋል።
ሌሎች መሰናዶዎች
በኒውሮሳይንስና ጥበብ ላይ ያተኮረ ልዩ ዝግጅት የፊታችን ሰኞ ሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ሊደረግ ነው፡፡ በዚህ ልዩ መርሐ-ግብር ላይ “ሲናፕስ ኢትዮጵያ” በይፋ ሊጀመር እንደሆነ አዘጋጆቹ ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል። “ሲናፕስ በኒውሮሳይንስ አለም እጅግ መሰረታዊ ፅንሰ-ሀሳብ ነው። ሁለት ነርቭ ሴሎች ተገናኝተው መረጃ የሚለዋወጡበት ድልድይ ማለት ነው። ይህንን መነሻ በማድረግ፣ ሲናፕስ ኢትዮጵያ በሀገራችን የመጀመሪያው በኒውሮሳይንስ ላይ ያተኮረ የህዝብ ንግግርና ውይይት መርሃ ግብር ነው። በመርሃ ግብሩም ስለ ኒውሮሳይንስ የቅርብ ጊዜ ዕውቀቶችና ምርምሮች በመድረኩ ይቀርባሉ” በማለት አዘጋጆቹ ለመገናኛ ብዙሃን አሳውቀዋል፡፡
አዘጋጆቹ የኒውሮሳይንስ ዕውቀት በጤና፣ በትምህርት እና በሌሎችም የህይወታችን ዘርፎች ላይ እንዴት ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ጥናቶች እንደሚቀርቡ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም “በተመራማሪዎችና በዝግጅቱ ታዳሚዎች መካከል የልምድ ልውውጥና አዲስ ግንኙነት ይፈጠራል። ጎን ለጎን ስነ-ጥበባዊ ዝግጅቶችም ይቀርባሉ። የሳይንስና የኪነ-ጥበብ ውህደት በፈጠረው ልዩ ድባብ እንዝናናለን” ሲሉም አስታውቀዋል።
ቴአትር
በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ ከሚታዩ ቴአትሮች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ ቅዳሜ 8:30 ሰዓት የቅርብ ሩቅ እና 11፡30 ሰዓት ባሎችና ሚስቶች፤ እሁድ በ8፡00 ሰዓት 12ቱ እንግዶች፣ 11፡30 ሰዓት እምዬ ብረቷ በብሔራዊ ቴአትር ይታያሉ፡፡ በቀጣይ ቀናት ይኼው ቀጥሎ ማክሰኞ በ11፡30 ሰዓት ሶስቱ አይጦች፣ ረዕቡ በ11፡30 ሰዓት የቅርብ ሩቅ፣ ሐሙስ 11:30 ሰዓት ሸምጋይ፣ አርብ በ11፡30 ሰዓት የሕይወት ታሪክ በዚሁ ቴአትር ቤት ለጥበብ አፍቃሪያን ለዕይታ ይቀርባሉ፡፡
በአብርሃም ገብሬ