አዲስ አበባ ከተማን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ስማርት ሲቲ ለማድረግ በርካታ ፕሮጀክቶች እውን እየተደረጉ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልፀዋል።
ጥራትና ብቃት በትምህርት ሴክተሩ የተገለጠበት ወቅትም መሆኑን ያብራሩት ኃላፊው፣ ባለፉት የለውጥ አመታት የትህርት ቤቶችን ተደራሽነት ለማስፋትና ለማረጋገጥ ከነባር ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ 1 መቶ 10 አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ወደ አገልግሎት መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ከ3 መቶ 34 በላይ የተማሪ መመገቢያ አዳራሾችን ጨምሮ ከ30 ሺህ በላይ የመማሪያ ክፍሎችን እውን ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ይህም ስታንዳርዱን በመጠበቅና በማሟላት የተማሪ ጥምርታን ለማረጋገጥ ያስቻለ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በመገባደድ ላይ በሚገኘው የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት 150 የትምህርት ተቋማት ከ5.2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎባቸው ገቢራዊ የሆነበት አመት መሆኑን ጠቅሰው፣ የአመራርና የሠራተኛ ቁርጠኝነት እንዲሁም ብቃት ያላቸው የመሞህራን ስምሪት ለትውልድ ቀረፃ የተሰጠውን ትኩረት በከፍተኛ ሁኔታ ያመላከተ ነው ብለዋል።
ከተገነቡ 150 ትምህርት ቤቶች መካከል 14ቱ በኮሪደር ልማትና በወንዝ ዳርቻ የተነሱ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ ሄዱበት የጋራ መኖሪያ አካባቢ የተገነቡ ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

ይህም ተማሪዎች ወደውና ፈቅደው በትምህርት ገበታቸው እንዲገኙ በማስቻል ትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ የበቃ ትውልድ በመፍጠር የጎላ ሚና እንደሚጫወት አመላክተዋል።
መንግስት ተደራሽ መሆን በማይችልባቸው አከባቢዎች በትምህርት ለትውልድ እንቅስቃሴ ባለፉት 2 አመታት ብቻ 10 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የትምህርት ተቋማትን ደረጃ ከፍ ለማድረግ ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ገልፀዋል።
ቀድሞ በደረጃ አንድ የነበሩ ተቋማት ወደ ደረጃ ሶስት ከፍ እንዲሉ ያስቻለና፣ በበጀት ዓመቱ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት በአደረጃጀት በመሠረተ ልማት ተቋማቱ ከደረጃ አራት በላይ መሆን እንዲችሉ በር የከፈተ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አጠቃላይ በከተማ አስተዳደሩ የተሰጠው ትኩረት በተማሪዎች ውጤትና ስነ ምግባር ላይ ተጨባጭ ለውጥ፣ የመማር ፍላጎትና መሻሻል ያመጣ ወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት እንደሆነ ሙላቱ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
በከተማ አስተዳደሩ የሚደረጉ የምገባ፣ የተማሪ ደንብ ልብስና የደብተር ድጋፎች ከግል ትምህርት ቤቶች ጋር ተቀራራቢ ውጤት እንዲኖር በማስቻሉ፣ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ተመራጭ እንዲሆኑ አስችሏልም ብለዋል።
የነቃ የበቃ ትውልድ ከመፍጠር ባሻገር ከትምህርት አገልግሎቱ ጎን ለጎን በስፖርት፣ በከተማ ግብርናና በመሳሰሉት ቅይጥ ማህበራዊ አገልግሎቶን መስጠት የሚችሉ ተቋማት እውን ማድረግ ተችሏልም ብለዋል።
በሚካኤል ህሩይ