በ2018 በጀት ዓመት ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማስመዝገብ በትኩረት እንደሚሰራ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዘዳንቱ የክልሉን መንግስት የ2018 በጀት አመት ዕቅድ ለጨፌ ኦሮሚያ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፣ ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማስመዘገብ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ለዚህም ይረዳ ዘንድ በተለይ የግሉ ኢንቨስትመንት ድርሻ ላቅ ያለ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል።
የክልሉ አስተዳደር በ2018 በጀት አመት 10ሺ 500 አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ወደ ስራ ለማስገባት እንደሚሰራም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች እስከ 1 ሚሊዮን የስራ ዕድል እንደሚፈጥሩም ተመላክቷል።
በተጨማሪም የከተማ ነዋሪዎችን ኑሮ ለማሻሻል የተጀመሩ የከተማ ግብርና ኢኒሼቲቮችን በ2018 በጀት አመት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል።
በትምህርት ዘርፉም አዳዲስ ኢኒሼቲቮችን በማካተት ለተሻለ ውጤት እንደሚሰራ የጠቆሙት አቶ ሽመልስ፣ 2ሺ 853 ቡኡረ ቦሩ ትምህርት ቤቶች፣ 170 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም 22 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት የትምህርት ተደራሽነትን ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።
በአጠቃላይ ከቡኡረ ቦሩ እስከ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪዎች ተሳትፎን 13.05 ለማድረስ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በሀብታሙ ሙለታ