በቬትናም የጎብኚዎች ጀልባ ሰጥማ የ37 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለጸ

You are currently viewing በቬትናም የጎብኚዎች ጀልባ ሰጥማ የ37 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለጸ

AMN – ሐምሌ13/ 2017 ዓ.ም

በቬትናም ሃሎንግ ቤይ በተሰኘው መዳረሻ በተከሰተ ድንገተኛ ማዕበል የጎብኚዎች ጀልባ በመስጠሟ የ37 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገልጿል።

አደጋው የተከሰተው በቬትናም ሰሜናዊ ክፍል በሚገኘው እና በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት በተመዘገበው ሃሎንግ ቤይ በተሰኘው መዳረሻ መሆኑም ተመላክቷል።

በሥፍራው ድንገት የጣለው አውሎ ነፋስ የቀላቀለ ከባድ ዝናብን ተከትሎ የሰጠመችው ጀልባ፣ 48 መንገደኞችን እና 5 የጀልባዋ ሰራተኞችን አሳፍራ እንደነበር ተገልጿል፡፡

አደጋው ከደረሰባቸው ሰዎች አብዛኞቹ የቬትናም ዜጎች ሲሆኑ፣ ከመዲናዋ ሃኖይ የመጡ ቤተሰብ የሆኑ ተጓዦች እና ከ20 በላይ ልጆች እንደነበሩም ተዘግቧል።

የድንበር ላይ ጠባቂዎች 11 በህይወት ያሉ ሰዎችን መታደጋቸውን እና 34 አስከሬኖችን ማግኘታቸውን ዘገባው አያይዞ ገልጿል፡፡

የነፍስ አድን ሰራተኞችም የደረሱበት ያልታወቁ ስምንት ሰዎችን ፍለጋ መቀጠላቸው ተነግሯል፡፡

የሃሎንግ ቤይ ጽሕፈት ቤት ሰራተኛ ትራን ትሮንግ ሃንግ እንደገለጹት፣ አውሎ ነፋሱ የጀመረው በሀገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ ነበር፡፡

በወቅቱ አውሎ ነፋስ እና መብረቅ የቀላቀለ በውስጡም ወፋፍራም በረዶ ያዘለ ከባድ ዝናብ ይጥል እንደነበር አንስተዋል፡፡

በህይወት የተረፈ አንድ የ10 ዓመት ልጅ ለሀገሪቱ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን እንደገለጸው፣ ረዥም ትንፋሽ በመውሰድ በዋና መቆየቱን እና በመሃልም የድረሱልኝ ድምጽ ሲያሰማ እንደነበር የገለጸ ሲሆን፣ ከዚያም ወታደሮች በጀልባ ደርሰው እንዳወጡት ተናግሯል፡፡

የቬተናም ጠቅላይ ሚኒስተር ፋም ሚን፣ በአደጋው የተሰማቸውን ሀዘን የገለጹ ሲሆን፣ ቤተሰባቸውን እና ወዳጆቻቸውን ላጡ ወገኖች ሁሉ መጽናናትን ተመኝተዋል።

የሀገሪቱ የመከላከያ እና የህዝብ ደህንነት ሚኒስቴሮችም አፋጣኝ የማፈላለግ እና የነፍስ አድን ሥራ እንዲያከናውኑ ትዕዛዝ መስጠታቸውን አር ቲ ኢ ዘግቧል፡፡

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review