በክልሉ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች የመደበኛ ፍርድ ቤቶችን የስራ ጫና መቀነስ መቻላቸውን አቶ ገዛሊ አባሲመል ገለጹ

You are currently viewing በክልሉ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች የመደበኛ ፍርድ ቤቶችን የስራ ጫና መቀነስ መቻላቸውን አቶ ገዛሊ አባሲመል ገለጹ

AMN – ሐምሌ 13/ 2017 ዓ.ም

በኦሮሚያ ክልል ባህላዊ ፍርድ ቤቶች በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ላይ የሚታይን የስራ ጫና በመቀነስ ማገዛቸውን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ገዛሊ አባሲመል ገልጸዋል።

የጨፌ ኦሮሚያ 6ኛ የስራ ዘመን 4ኛ ዓመት 9ኛ መደበኛ ጉባዔ 2ኛ ቀን ውሎ በአዳማ ገልመ አባ ገዳ እየተካሄደ ነው።

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ገዛሊ አባሲመል ለጨፌው ባቀረቡት ሪፖርት እንዳሉት፣ የባህላዊ ፍርድ ቤቶች ወደ ስራ መግባት በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ላይ የነበረውን የስራ ጫና ቀንሰዋል።

ባህላዊ ፍርድ ቤቶቹ በቅርበት መገኘታቸው ህብረተሰቡ ፈጣንና ቀልጣፋ ፍትህ እንዲያገኝ ማስቻላቸውንም ጠቁመዋል።

ለአብነትም በበጀት ዓመቱ ለባህላዊ ፍርድ ቤቶች የቀረቡ ከ443 ሺህ በላይ ጉዳዮች እልባት ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ውስጥ 16 ሺህ 829 ጉዳዮች በይግባኝ የቀረቡ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ባህላዊ ፍርድ ቤቶች የተገልጋዮችን የፍትህ ተደራሽነት እውን ከማድረግ ባለፈ ዜጎችን ከእንግልትና ወጪ መታደግ ማስቻላቸውን አመላክተዋል።

የፍትህ ተደራሽነቱን ለማስፋትም በክልሉ 5 ሺህ 678 የባህላዊ ፍርድ ቤቶች (ጋዲሳ ሃቃ) ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የባህላዊ ፍርድ ቤቶችን የህግ ግንዛቤ ለማሳደግም የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።

በዚህም በቀጣይ የባህላዊና ዘመናዊ ፍርድ ቤቶችን ቅንጅት በማጠናከር ለዜጎች የተሻለ የፍትህ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በትብብር ይሰራል ብለዋል።

በክልሉ በመደበኛና ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ለዜጎች ፈጣንና ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎቶች ተደራሽ ለማድረግ የተዘረጉ አሰራሮችና ሪፎርሞች ከክልሉ ውጭ ላሉትም ልምድ እንዳካፈሉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review